ትውልደ ሶማሊያዊቷ የአሜሪካ ምክር ቤት አባል በፖሊስ ታሰረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትውልደ ሶማሊያዊቷ የአሜሪካ ምክር ቤት አባል ኢልሃን ኦማር ከሌሎች ባልደረቦቿ ጋር በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተሳትፋ በፖሊስ በቁጥጥር ስር ዋለች።
በቅርቡ በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጽንስ ማቋረጥ እንዲታገድ የተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በተደረገ ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ኢልሃን ኦማርን ጨምሮ 17 የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት በፖሊስ ተይዘዋል።
ታዋቂዎቹ የዴሚክራቲክ ፓርቲ አባላት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ ኢልሃን በፖሊስ ከሌሎች ጋር መያዟን ትዊተር ላይ ባሰፈረችው መልዕክት አሳውቃለች።
“በሕዝባዊ ሰልፍ ላይ እየተሳተፍኩ ሳለ በፖሊስ ተይዣለሁ። የተያዝኩትም ከሌሎች የምክር ቤት አባላት ጋር ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውጪ ነው” ብላለች በትዊተር መልዕክቷ።
የአሜሪካ ኮንግርስ አባል የሆነችው ኢልሃን ኦማር ጨምራም፣ አሜሪካውያን ሴቶች ጽንስ የማቋረጥ መብታቸው እንዲከበር ጥረቷን እንደምትቀጥል አመልክታለች።
“በሥነ ተዋልዶ ጤናችን ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት በተመለከተ ድምጼን ለማሳማት የምችለውን ሁሉ ማድረጌን እቀጥላለሁ።”
ትዊተር ላይ በወጣ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ፣ ኢልሃንና ሌሎች የምክር ቤት አባላት ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፊትለፊት እጃቸው የታሰረ በማስመሰል ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ታይተዋል።
የአሜሪካ ፖሊስ 17 የአሜሪካ ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ 35 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አረጋግጧል።
“የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ማገድ ሕገወጥ ድርጊት ነው። ሰልፈኞቹ መንገድ መዝጋት በጀመሩበት ወቅት ፖሊስ ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ ቢሰጥም የሚሰማው አላገኝም” ሲል የእርምጃውን ምክንያት በትዊተር ላይ ገልጿል።
የምክር ቤት አባላቱ ለእስር የተዳረጉበት የተቃውሞ ሰልፍ በቅርቡ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለዘመናት ተግባራዊ የነበረውን ጽንስ የማቋረጥ መብት በመላው አገሪቱ ማገዱን ተከትሎ ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1973 ወዲህ ጽንስ የማቋረጥ መብትን የፈቀደው ሕግ የቀለበሰው ውሳኔ ከአንድ ወር በፊት መተላለፉን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውጪ በመሰብሰብ አስካሁን ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ይገኛሉ።












