አዲሱ የሶማሊያ አስተዳደር ወታደሮቼ በኢትዮጵያ ጦርነት አልተሳተፉም አለ

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ አብዲካሪም አሊ ካር

የፎቶው ባለመብት, Somali National TV

የምስሉ መግለጫ, የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ አብዲካሪም አሊ ካር
ታትሟል

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ አስተዳደር በኤርትራ ስልጠና ሲወስዱ የነበሩት የሃገሪቱ ወታደሮች በኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት አልተሳተፉም አለ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የትግራይ ኃይሎች የሶማሊያ ወታደሮች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከፌደራል መንግሥቱ ጎን ተሰልፈው ተዋግተዋል ሲሉ ነበር።

ይሁን እንጂ የቀድሞ የሶማሊያ መንግሥት ፕሬዝዳንት አስተዳደርም ሆነ አዲሱ መንግሥት፤ የሶማሊያ ወታደሮች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት አልተሳተፉም ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም የሶማሊያ ወታደሮች በትግራዩ ጦርነት ውስጥ ተሳትፈዋል የሚለውን ክስ ማስተባበሉን በወቅቱ ብሉምበርግ ዘግቦ ነበር።

ትናንት ሐምሌ 12/2014 ዓ.ም. የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ፤ የሶማሊያ ወታደሮች በኢትዮጵያው ጦርነት ተሳትፈዋል መባሉ ያልተረጋገጠ መረጃ ነው ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አብዲካሪም አሊ ካር፤ “ካልተጨበጠ መረጃ በቀር የሶማሊያ ወታደሮች በኢትዮጵያው ጦርነት ተሳትፈዋል የሚል መረጃ  ተመልክታችኋል?” ሲሉ በጋዜጣዊመግለጫው ላይ ጠይቀዋል።

የሶማሊያ ወታደሮች በኤርትራ

ባለፉት ሦስት ዓመታት በሶማሊያ ፖለቲካ ውስጥ አወዛጋቢ ሆኖ ከቆዩት ጉዳዮች መካከል ወደ ኤርትራ ተልከዋል የተባሉት በሺህዎች የሚቆጠሩሶማሊያውያን ወታደሮች አንዱ ነው።

ሶማሊያውያኑ ወታደሮች፣ መቼ እና በምን ሁኔታ ወደ ኤርትራ እንደሄዱ ሳይገለጽ ቆይቶ፤ የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ጉብኝትን ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት ሐምሌ 03/2014 ዓ.ም. ለሦስት ዓመታት ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስዱ የነበሩት የሶማሊያ ወታደሮች ተመርቀዋል ብሏል።

ተቀናቃኞች በበኩላቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ወታደሮቹን ወዳልታወቀ ስፍራ ልከው በኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት ማግደዋቸዋል በሚል ሲወቅሷቸው ቆይተዋል። የወታደሮቹ ቤተሰብ አባላትም ስለልጆቻቸው ሁኔታ በመጠየቅ መንግሥትን አስጨንቀው ነበር።

 ትናንት የፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ፤ የሶማሊያ ወታደሮች በኤርትራ የቆዩት ሶማሊያ የሚጠበቅባትን ገንዘብ መክፈል ባለመቻሏ ወታደሮቹ እንደመያዣነት ተይዘው ነው የሚባለውም ሐሰት ነው ብለዋል።

“ሐሰት ነው። ወታደሮቹ እንደመያዣነት አልተያዙም። ለማንም መክፈል ያለብን ገንዘብ የለም። እንደ ተርኪዬ፣ ኡጋንዳ እና ኢትዮጵያ ያሉ ሃገራት የሶማሊያንወታደሮች ያሰለጥናሉ። ስልጠና የሚሰጣቸው ለገንዘብ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በኤርትራ የሚገኙት የሶማሊያ ወታደሮች ብዛት 5 ሺህ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሞቃዲሹ መንግሥት ወታደሮቹን ወደ ሃገር ቤትለመመለስ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

“ልጆቻችን የት ናቸው?”

ሶማሊያውያን ወታደሮች በትግራይ ጦርነት ተሳትፈዋል የሚል ሪፖርት በስፋት መውጣቱን ተከትሎ ወላጆቻቸው "ልጆቻችንን የት ናቸው? ልጆቻችንን አምጡ" በሚል በሞቃዲሾ እና በሌሎች ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ማካሄዳቸው በስፋት ተዘግቦ ነበር።

ወታደሮቹ እአአ በ 2019 ላይ ወደ ኤርትራ የተላኩ መሆናቸውን ሪፖርቶች ያመላከቱ ሲሆን፣ ወታደሮቹ ሶማሊያን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ኳታር ለምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ በጥበቃነት እንደሚሠሩ ተነግሯቸውነበር ተብሏል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ያነጋገራቸው አሊ ጂማክ ዱዲ የተባሉ አባት፤ ልጃቸው ከሃገር የወጣውኳታር ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ በጥበቃ ሠራተኝነት ለመቀጠር በተነገረው መረጃ መሠረት እንደሆነበወቅቱ አስረድተዋል።