የሩሲያ ሚሳኤል የዩክሬን ግድብ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነዋሪዎች እንዲወጡ ማሳሰቢያ ተሰጠ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያ ሚሳኤል ዋነኛ የሚባል የውሃ ማጠራቀሚያ ግድብ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ በደቡባዊ ዩክሬን ከተማ የሚገኙ ባለስልጣናት ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ አሳሳቡ።
ጥቃቱ ክሪቭ ሪህ በተባለችው ከተማ የጎርፍ መጥለቅለቅ ያስከተለ ሲሆን ሁለት ወረዳዎችም በከፍተኛ አደጋ ላይ ናቸው ሲሉ የከተማዋ አስተዳዳሪ ኦሌክሳንደር ቪልኩል ረቡዕ ዕለት አስጠንቅቀዋል።
ባለስልጣናቱ እንደተናገሩት ግድቡን ጥሶ በሰኮንድ 100 ሜትር እየፈሰሰ ያለው ውሃ የኢንሁሌትስ ወንዝን በአደገኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጎታል።
ሩሲያ በግድቡ ላይ ያደረሰችውን ጥቃት ዩክሬን በቅርቡ ለወሰደችው የመልሶ ማጥቃት የበቀል እርምጃ ነው ስትል ፈርጃዋለች።
ረቡዕ ዕለት ካራቹኒቭስኬ ግድብ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሩስያን “አሸባሪ መንግሥት” ሲሉ ጠርተውታል።
ጎርፉ ያጥለቀለቃት ክሪቪ ሪህ የተወለዱት ፕሬዚዳንቱ “ንጹሃንን የምትዋጉ ደካማዎች ናችሁ” በማለት ረቡዕ ምሽት ባደረጉት ንግግር ወርፈዋቸዋል።
“የጦር ሜዳውን አምልጠው ከሩቅ ቦታ ሆነው ጉዳት ለማድረስ የሚሞክሩ አጭበርባሪዎች” ሲሉም አክለዋል።
የፕሬዚዳንቱ ይህ ንግግር ጦራቸው በዩክሬን ሰሜናዊ ምስራቅ ካርኪቭ ግዛት መልሶ በማጥቃት ባደረገው ዘመቻ የተጎናጸፈውን ስኬቶች ያመላከተ ነው።
የዩክሬን ጦር የተወሰኑ ግዛቶች መልሶ ሲቆጣጠር የሩስያ ወታደሮችም ለማፈግፈግ ተገደዋል።
ዩክሬን ከሩሲያ የተወሰዱብኝን መልሼ ተቆጣጥሬያቸዋለሁ የምትላቸውን ግዛቶች በተመለከተ ቢቢሲ ማረጋገጥ አልቻለም።
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በንግግራቸው ግድቡ “ምንም አይነትወታደራዊ ጠቀሜታ የለውም" ብለዋል።
ከሩሲያ ወረራ በፊት 600 ሺህ ህዝብ በሚኖርባት ከተማ ጥቃቱን ተከትሎም የውሃ አቅርቦት ችግር ገጥሟል።
ሩሲያ ደርሷል ስለተባለው ጥቃት ያለችው ነገር የለም።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በምስራቃዊ ዩክሬን የሚገኝ የኃይል ማመንጫ ኢላማ ማድረጉን የሩስያ ጦር ሃይል ቀደም ብሎ አምኗል።












