የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት የመኪና አደጋ አጋጠማቸው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ትናንት የመኪና አደጋ እንዳጋጠማቸው ቃል አቀባያቸው ተናገሩ።
ይሁንና አደጋው በፕሬዝዳንቱ ላይ ያስከተለው ይህ ነው የሚባል ጉዳት የለም።
አንድ የመንገደኞች መኪና እርሳቸው ከነበሩበት መኪና፣ እንዲሁም እሳቸውን አጅቦ እየተጓዘ ከነበረ ሌላ የደኅንነት ተሽከርካሪ ጋር የተጋጨው ዘለንስኪ ኢዚዮም ከተማን ጎብኝተው ከተመለሱ በኋላ ነው።
አደጋው የደረሰውም ኪየቭ ከተማ ውስጥ እንደሆነም ተነግሯል።
እርሳቸው ከነበሩበት መኪና ጋር የተላተመው ተሽከርካሪ ወዲያውኑ በአምቡላንስ ከአካባቢው እንዲርቅ ተደርጓል።
ጉዳዩ አጋጣሚ ነው ወይስ የግድያ ሙከራ በሚለው ዙርያ ምንም የተባለ ነገር የለም።
ሆኖም ነገሩ በጸጥታ አካላት ተይዞ ምርመራ ላይ እንደሆነ ተመላክቷል።
የ44 ዓመቱ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ኢዝዮም የተባለችውን ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላትን ከተማ ወታደሮቻቸው ከሩሲያ ነጻ ማድረጋቸውን ተከትሎ ወደዚያው አቅንተው ነበር።
በዚያ ያሉ ወታደሮቻቸውን አነቃቅተው ወደ ዋና ከተማ ኪየቭ ከደረሱ በኋላ ነው ይህ የመኪና ግጭት የተከሰተው።
ዘለንስኪ በኢዚዮም ከተማ የአገራቸው ባንዲራ ዳግም ከፍ ብሎ ሲውለበለብ በሥነ ሥርዓቱ ተገኝተው ነበር።
የዩክሬን ወታደሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሩሲያ ተይዘውባቸው የነበሩ በርካታ አካባቢዎችን ነጻ እያወጡ እንደሆነ እየተዘገበ ይገኛል።












