ከ770 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ አደንዛዥ ዕጽ በአዲስ አበባ አየር ማረፊያ ተያዘ

ታትሟል

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን 97 ኪሎ ግራም የሚመዝንና ከ773 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ የሚያወጣ የኮኬይን አደንዛዥ ዕጽ ቦሌ አየር ማረፊያ ውስጥ መያዙን አስታወቀ።

እንደ ኮሚሽኑ መረጃ ይህ በአዲስ አበባ አየር ማረፊያ ውስጥ የተያዘው አደንዛዥ ዕጽ፣ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተያዙ ከፍተኛ መጠን ካላቸው አደንዛዥ ዕጾች መካከል አንዱ ሊባል የሚችል ነው።

97.48 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ይህ የኮኬይን አደንዛዥ ዕጽ የተያዘው ከኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ወደ አዲስ አበባ በመጣች ግለሰብ ሻንጣ ውስጥ ነው።

ግለሰቧ አንድ መቶ ኪሎ ግራም የሚጠጋው ዕጽ በሁለት ሻንጣዎች ውስጥ እኩል በ49 ኪሎ ግራም ገደማ ይዛ ለማሳለፍ ስትሞክር በጉምሩክ ኮሚሽን ኤርፖርት ቅርንጫፍ አባላት በቁጥጥር ስር መዋሏ ተነግሯል።

ተጠርጣሪዋ ቀረጥና ታክስ የሚከፈልበትን እቃ ያልያዙ መንገደኞች በሚያልፉበት ዝቅተኛ የስጋት ደረጃ ወይም አረንጓዴ የጉምሩክ ማለፊያ መስመር በኩል ልታልፍ ስትል መያዟ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን 97 ኪሎ ግራም የሚመዝነውንና በገንዘብ ቢተመን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ሊያወጣ የሚችለውን አደንዛዥ ዕጽ ስታዘዋውር ተይዛለች ስለ ተባለችው ግለሰብ ዜግነትና ማንነት የሰጠው መረጃ የለም።

ጉምሩክ ኮሚሽን እንዳለው ግለሰቧ ዕጹን በእያንዳንዱ ሻንጣ 48.62 እና 48.86 ኪሎ ግራም በማድርግ እቃዎች በሚፈተሹበት መሳሪያ እንዳይለዩ ለማድረግ መጽሐፍ በማስመሰል እና በአልሙኒዬም ፎይል በመጥቅለል ለመደበቅ ሞክራለች ተብሏል።

በሻንጣዎቹ ላይ በተደረገው ፍተሻ 100 ኪሎ ሊሞላ ከሦስት ኪሎ ያነሰ የጎደለው ኮኬይን የተባለው ዕጽ መያዙንና ይህም በምርመራ መረጋገጡን ኮሚሽኑ አሳውቋል።

ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው አደንዛዥ ዕጽ ከጉምሩክ ቁጥጥር አልፎ ቢገባ ወደ 773 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ግምት እንደነበረው የተጠቀሰ ሲሆን፤ ከባድ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና የደኅንነት ችግር ሊያስከትል ይችል እንደነበር ተገልጿል።

ከዚህ በፊት ከምዕራብ አፍሪካ አገራት እንዲሁም ከእስያ አገራት በሚጓዙ መንገደኞች እጅ ላይ የተለያየ መጠን ያላቸው አደንዛዥ ዕጾች በሕግ አስከባሪዎች ቁጥጥር ስር መዋላቸው የተነገረ ሲሆን፣ ይህ የአሁኑ ግን ከፍተኛ መጠን ካላቸው ውስጥ የሚጠቀስ ነው።