የቀድሞ የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ሲልቪዮ ቤርለስኮኒ ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
አወዛጋቢው የቀድሞው የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ሲልቪዮ ቤርለስኮኒ በ86 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የጣሊያን መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
ከወሲብ ቅሌት እና ሙስና ወንጀሎች ጋር ስማቸው በስፋት ተያይዞ ይነሳ የነበሩት ቤርለስኮኒ ዛሬ ሚላን በሚገኝ ሆስፒታል ሕይወታቸው ማለፉ ተዘግቧል።
ለቤርለስኮኒ ሞት ምክንያት የሆነው የጤና እክል ምን እንደሆነ በይፋ ባይነገርም ሚያዚያ ወር ላይ ከደም ካንሰር ጋር በተያያዘ የሳምባ መቆጣት አጋጥሟቸው ሆስፒታል ገብተው ነበር።
የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ በሚያደርጉት ጥረት የሚታወቁት ቢሊየነሩ እአአ 1994 ላይ የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው እስ 2011 ድረስ ለ17 ዓመታት መርተዋል።
ቤርለስኮኒ ሀብት እና ሚዲያን በመጠቀም በፖለቲካው ዓለም እራሳቸውን ተጽእኖ ፈጣሪ ማድረግ የቻሉ ወደ ስልጣንም ከመጡ በኋላ ፖለቲካዊ ስልጣናቸውን በመጠቀም የግል ንግዳቸውን አጠናክረዋል የሚል ተቀናቃኞቻቸው የሰላ ትችት ይሰነዝሩባቸዋል።
የቤርለስኮኒ ፓርቲ ፎርዛ ኢታሊያ መስከረም ወር ላይ ከተደረገው ምርጫ በኋላ ከጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂ ሜሎኒ ጋር ጥምር መንግሥት ፈጥሯል።
የቤርለስኮኒን ሕልፈተ ዜናን ተከትሎ የጣሊያን መከላከያ ሚንስትር ጉኢዶ ክሮሴቶ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ሞት፤ ‘ትልቅ ክፍተት ፈጥሯል’ ብለዋል።
የቀድሞ መሪ ብዙዎችን በማያጠቃው የደም ካንሰር አይነት ሲሰቃዩ የቆዩ ሲሆን ለሞታቸው ምክንያት የሆነው ምን እንደሆነ እስካሁን አልተገለጠም።
እአአ 1936 ሚላን ከተማ የተወለዱት ቤርለስኮኒ ወደ ፖለቲካው ዓለም ከመግባታቸው በፊት በንፋስ ኃይል የሚያጸዱ ማሽኖችን ይሸጡ የነበረ ሲሆን ከዚያም በኋላ የግንባታ ኩባንያ አቋቁመው ነበር።
በመቀጠል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ባለቤት በመሆን ትልቅ ሃብት ማፍራት ችለዋል።
ቤርሌስኮኒ ወደ ፖለቲካው ዓለም ከመግባታቸው በፊት የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ገብቶ የነበረውን ኤሲ ሚላን የእግር ኳስ ክለብን በመታደግ የቡድኑ ባለቤት ከሆኑ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት መታወቅ ችለዋል።












