የፊልም ባለሙያው ዮናስ ብርሃነ መዋ ከቀናት እስር በኋላ ተለቀቀ

የፎቶው ባለመብት, LEZA AWARD/SOCIAL MEDIA
ባለፈው አርብ ሌሊት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረው የፊልም ባለሙያው ዮናስ ብርሃነ መዋ ከእስር መለቀቁን የሥራ ባልደረቦቹ ገለጹ።
ለሁለት ቀናት በእርስ ላይ የቆየው ዮናስ ባለፈው ቅዳሜ ፍርድ ቤት ቀርቦ በገንዘብ ዋስ እንዲለቀቅ የፈቀደለት ቢሆንም፣ ለተጨማሪ ቀናት በእስር ላይ ቆይቶ ነው ሰኞ ሰኔ 05/2015 ዓ.ም. እኩለ ቀን አካባቢ የተለቀቀው።
በእስር ላይ ሳለ ሰኞ ጠዋት ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዮናስ ብርሃመ መዋ የቅርብ ጓደኞች በእስር ላይ የሚቆይበት በቂ ምክንያት ስለሌለ ይለቀቃል ብሎ ቤተሰቡ እየጠበቀ መሆኑን ገልጸው ነበር።
የፊልም ባለሙያ እና የጉማ የፊልም ሽልማት መሥራች ዮናስ ብርሃነ መዋ ከቀናት በፊት ብዙ ባነጋገር ክስተት በቁጥጥር ሥር መዋሉ ይታወሳል።
የፊልም ባለሙያው ዮናስ ብርሃነ መዋ ከሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ በኋላ አርብ ሰኔ 02/2015 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውሏል።
አርብ ምሽት በጉማ የፊልም ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ታድመው የነበሩ የዐይን እማኞ ዮናስ በቁጥጥር ሥር የዋለው ሲቪል በለበሱ የመንግሥት ደኅንነት ስዎች መሆኑን ተነግሮ ነበር።
ዮናስ ቅዳሜ ጠዋት ፍርድ ቤት ቀርቦ በዋስ እንዲፈታ ቢወሰንም በተመለዶ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተብሎ ወደሚጠረው እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መዘዋወሩን የቤተሰብ አባሉ ገልጸዋል።
ዮናስ ብርሃነ በምን ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ቢቢሲ የዮናስ እስር ምክንያትን በተመለከተ የአዲስ አበባ ፖሊስን ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት በቂ ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ የፊልም ባለሙያውን እስር በተመለከተ መረጃ አሰባስበው እንደሚገልጹ ቃል ገብተው ለጊዜው ግን እስሩን በተመለከተ መረጃው እንደሌላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቤተሰብ እና ጓደኞቹ እንደሚሉት ዮናስ በቁጥጥር ሥር የዋለው በጉማ የፊልም ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ አንዲት ታዳሚ በቀረበችበት ሁኔታ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በቴሌቪዥን ፕሮግራሟ እና ቲክቶክ ላይ ‘የልጅ ማኛ’ በሚል ስም የምትታወቀው ፍላጎት አብርሃም በሜካፕ እና በአለባበሷ ያስተላለፈችው መልዕክት የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል።
ፍላጎት አብርሃም በሜካአፕ ግንባሯ ላይ በጥይት የተመታች፤ አፏ እንዳትናገር ደግሞ ከንፈሯን የተሰፋች በማስመሰል የኢትዮጵያ ሰንደቅ ከለበሰችው ነጭ ቀሚስ ስር አድርጋ በጉማ የፊልም ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝታለች።
ይህ የፍላጎት አብርሃም ምስልም የጉማ የፊልም ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ሳይጠናቀቅ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተዘዋውሯል።
የፊልም ባለሙያው ዮናስ ብርሃነ እስርም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ የቅርብ ጓደኞች፣ የቤተሰብ አባለት እና የሰብዓዊ መብት አመራር ገልጸዋል።
የዮናስ ወላጅ አባት ብረሃነ መዋ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ልጃቸው “ባላደረገው እና ሌሎች መብታችን ነው ብለው ባደረጉት ደርጊት ምክንያት ተጠርጣሪ ተደርጎ ለእስር ሲዳረግ ማየት ቅስም ይሰብራል ተስፋን ያጨልማል” ሲሉ ጽፈዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የፊልም ባለሙያው ዮናስ እስር ሕገ-ወጥ እና ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።
ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር) ዮናስ በቁጥጥር ሥር የዋለው በሌላ በቴሌቪዥን ሥራዎችን በምትታወቅ የጉማ አዋርድ ታዳሚ አድርጋ በቀረበችው የሥነ ሥበብ ሥራ ምክንያት ነው ካሉ በኋላ፣ “ይህም በነጻነት የመናገር አካል በመሆኑ የፊልም ባለሙያው ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቅ” ጠይቀዋል።
በጉማ የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ምን ተከሰተ?
በኢትዮጵያ ከሚታወቁት የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች የሽልማት መድረክ አንዱ የሆነው 9ኛው ጉማ የፊልም ሽልማት የተካሄደው ባለፈው ዓርብ ሰኔ 02/2015 ዓ.ም. ምሽት በስካይላይት ሆቴል ነበር።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ በተለያዩ ዘርፎች የፊልም ባለሙያዎች ሽልማቶችን ቢያሸንፉም ትልቁ ትኩረት ሆኖ የቆየው የሥነ-ሥርዓቱ ታዳሚ የነበረችው ፍላጎት አብርሃም በሜካፕ እና አለባበስ ያስተላለፈችው መልዕክት እንዲሁም የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ ዮናስ ብርሃነ እስር ነው።
የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱን ታድመው ከነበሩት መካከል አንዱ የነበረው በፍቃዱ አባይ ብዙ መነጋገሪያ የነበረችው ፍላጎት በሆቴሉ የተገኘችው የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ከተጀመረ በኋላ መሆኑን ያስታውሳል።
በፍቃዱ ፍላጎት ከማንም ጋር ሳትነጋገር ፎቶግራፍ ለሚያነሷት እና ቪዲዮ ለሚቀርጿት ብቻ ቆማ መልዕክቷን አስተላለፍ ብዙም ሳትቆይ አዳራሹን ለቅቃ መውጣቷን ይናገራል።
እንደ በፍቃዱ ከሆነ ዮናስ በእርግጠኝነት የፍላጎትን መምጣትም ሆነ መሄድን አልተመለከተም ነበር ይላል።
ፍቃዱ በስካይላይት ሆቴል አደራሽ እና በዙሪያው ሲቪል የለበሱ እንዲሁም ዩኒፎርም የለበሱ የፀጥታ ኃይሎች በብዛት እንደነበሩ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በዚህ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ የሚጋበዙ እንግዶች በተለያየ ዓይነት በዲዛይነር የተሰሩ ባሕላዊ እና ዘመናዊ አልባሳትን ለብሰው ይታደሙበታል።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መቃወምን የመሳሰሉ እና ሌሎች መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የሚውሉ አልባሳት እና የፊት ገጽታ ቅቦችን በመጠቀም የታደሙ ሰዎች ነበሩ።
ፍላጎት አብረሃም ማን ናት?
ፍላጎት አብረሃም በብዙዎች ዘንድ 471 ሺህ ተከታዮች ባሉት ‘Ye_lij_magna’ በሚለው የቲክቶክ አካውንቷ ትታወቃለች።
በቲክቶክ ላይ ከፍተኛ ዝናን ካገኙ ወጣት ሴቶች መካከል አንዷ የሆነችው ፍላጎት፤ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በመምህርነት እያገለገለች ሲሆን፣ በሂሳብ እና በንግድ የትምህር ዘርፎች የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ድግሪዋን አጠናቃ የሦስተኛ ዲግሪዋን በመሥራት ላይ ትገኛለች።
በአባይ ሚድያ ላይ እንዝርት የተሰኘ ፕሮግራም ከሁለት ዓመት በላይ በአዘጋጅነት እና በአቅራቢነት ሰርታለች።
በጉማ የፊልም ሽልማት ላይ የቀረበችበት ሁኔታ ፍላጎት በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ያደረጋት ሲሆን፣ ይህም ለሽልማቱ አዘጋጅ መታሰር ምክንያት እንደሆነ እየተነገረ ነው።
ቢቢሲ ፍላጎት አብረሃምን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ባይሳካም፣ በፖሊስ እየተፈለገች እንደሆነ የሚወጡ ይፋዊ ያልሆኑ መረጃዎች አሉ።












