ማንቸስተር ዩናይትድ ከማንቸስተር ሲቲ - የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምት

ሩበን አሞሪም በያዝነው የውድድር ዘመን ማንቸስተር ሲቲን ሁለት ጊዜ መርታት ችሏል። መጀመሪያ የስፖርቲንግ አሰልጣኝ ሳለ። ቀጥሎ ደግሞ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር።
ነገር ግን እሑድ በኦልድ ትራፈርድ የሚከናወነውን ጨዋታ በድል ያጠናቅቅ ይሆን?
"ዩናይትድ ጎል የማስቆጠር ችግር አለበት" ይላል የቢቢሲ ስፖርቱ ተንታኝ ክሪስ ሱተን። "ትልቁ ችግራቸው እሱ ነው። ቢሆንም የሲቲ የመከላከል አቅም ደግሞ ያጠራጥረኛል።"
ሱተን ይህን የሳምንቱን ተጠባቂ ጨዋታ ጨምሮ የ31ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችን ግምት እንዲህ አስቀምጧል።
ቅዳሜ

ኤቨርተን ከአርሰናል
ይህ ለአርሰናል ከባድ ግጥሚያ ይመስላል። ኤቨርተን ባለፈው ረቡዕ ከሊቨርፑል ጋር በነበራቸው ጨዋታ ጠንክረው ተከላክለዋል። ሲያጠቁም ያስፈራሉ።
ቡካዮ ሳካ ከጉዳት ተመልሶ ከፉልሀም በነበረው ጨዋታ ተሰልፏል። ነገር ግን በዚህ ጨዋታ ጋብርኤልን ጨምሮ የተወሰኑ ተከላካዮች ተጎድተዋል።
በዚያ ላይ አርሰናል በሚቀጥለው ማክሰኞ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከሪያል ማድሪድ ይጫወታል። ይህ ለመድፈኞቹ ግጥሚያው ፈታኝ እንዲሆን ያደርገዋል።
ምንም እንኳ አርሰናል በማሸነፉ ቀጥሎበት ሊቨርፑል ላይ ጫና እንዲያሳድር ብፈልግም ግምቴ ጨዋታው አቻ እንደሚጠናቀቅ ነው።
ግምት፡ 1 - 1
ክሪስታል ፓላስ ከብራይተን
ሁለቱም ቡድኖች በሳምንቱ አጋማሽ አስከፍተውኛል። ጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ፓላስ ከሳውዝአምፕተን አቻ ተለያይቷል። አስተን ቪላን ይረታል ብዬ የጠበቅኩት ብራይተን ደግሞ በሜዳው 3 ለምንም ተሸንፏል።
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ በተገናኙባቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አቻ ነው የተለያዩት። በዚህም ፍልሚያ አቻ ይወጣሉ ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ 1 - 1
ኢፕስዊች ከዎልቭስ
ኢፕስዊች ይህን ጨዋታ ካላሸነፉ የመውረዳቸውነ ገር የተረጋገጠ ይሆናል። በሳምንቱ አጋማሽ ወደ ቦርንመዝ አቅንተው ማሸነፋቸው ትልቅ ተስፋ ይሰጣቸዋል።
ኢፕስዊች 17ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ዎልቭስ ያላቸው የነጥብ ልዩነት 9 ቢሆንም በሚቀጥሉት 8 ቀሪ ጨዋታዎች ምን ሊፈጠር እንደሚችል አይታወቅም።
ባለፈው ታኅሣሥ በዎልቭስ ሜዳ ድል ቀንቷቸው ተመልሰዋል። በሜዳቸውም ሊሳካላቸው ይችላል።
ግምት፡ 2 - 1
ዌስት ሀም ከቦርንመዝ
ቦርንመዝ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ነው ማግኘት የቻለው። የሚያስደንቅ የውድድር ዘመን እያሳለፉ ነው። ከሊጉ አምስት ኃያላን ክለቦች ከሊቨርፑል በቀር ሁሉንም አሸንፈዋል።
ነገር ግን ከሰሞኑ አቋማቸው መዳከሙ አሳሳቢ ነው። ቦርንመዝ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በአውሮፓ ለመጨዋት እንዲያስችላቸው ይህን ጨዋታ ማሸነፍ አለባቸው።
ዌስት ሀም በሜዳው ብዙም እየተሳካለት አይደለም። ካለፉት አራት ጨዋታዎች ሶስቱን ተሸንፏል።
ብዙዎች ይህ ጨዋታ አቻ ይጠናቀቃል ቢሉም እኔ ግን ቦርንመዝ ያሸንፋል እላለሁ።
ግምት፡ 1 - 2
አስተን ቪላ ከኖቲንግሀም
ኖቲንግሀም ፎሬስት ድንቅ አቋም ላይ ነው። አስተን ቪላም እንደዛው። ቪላ በሁሉም ጨዋታዎች ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ችሏል።
በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል። በዚህኛውም ጨዋታ አሸናፈውን መገመት ይከብደኛል።
ፎሬስት በዚህ ጨዋታ ነጥብ ቢጥሉ እንኳ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እንደሚጫወቱ እርግጠኛ ነኝ።
በሳምንቱ አጋማሽ ዩናይትድን ባሸነፉበት ጨዋታ ትኩረታቸው ኳስ ይዞ መንቀሳቀስ ሳይሆን ውጤት እንደሆነ አሳይተዋል።
አስተን ቪላ በሻምፒዮንስ ሊግ እና በኤፍ ኤ ካፕ ጨዋታዎች እየተሳተፈ ነው። የጨዋታ መደራረብ ሁኔታዎችን ሊያከብደው ይችላል።
ግምት፡ 1 - 1
እሑድ

ብሬንትፈርድ ከቼልሲ
የቼልሲ ትልቁ ችግር ወጥ የሆነ አቋም አለመያዝ ነው። ሐሙስ ከቶተንሀም በነበራቸው ጨዋታ ድንቅ ነበሩ። በእሑዱ ጨዋታ ይህን እንመለከት ይሆን? እርግጠኛ አይደለሁም።
በያዝነው የውድድር ዘመን ግራ ካጋቡኝ ቡድኖች መካከል አንዱ ብሬንትፈርድ ነው። ምንም ቢሆን ጎል እንደሚያስቆጥሩ አምናለሁ።
ይህ ጨዋታ በጎሎች የተሞላ እንደሚሆን እምነት አለኝ። ቼልሲ ይህን ጨዋታ ካሸነፈ እስከ አምስተኛ ባለው ደረጃ እንዲያጠናቅቅ ሊያግዘው ይችላል። ነገር ግን ድል ይቀናዋል የሚል እምነት የለኝም።
ግምት፡ 1 - 1

ፉልሀም ከሊቨርፑል
ፉልሀም ወደ አንፊልድ አቅንቶ አንድ ነጥብ ይዞ መመለሱ አይዘነጋም።
ማክሰኞ ከአርሰናል ጋር በነበራቸው ጨዋታም ፈታኝ ነበሩ። ከሊጉ መሪ ሊቨርፑል ጋር የሚያደርጉት ጨዋታም እንዲሁ ከባድ እንደሚሆን እጠብቃለሁ።
ምንም እንኳ ፉልሀም ቀላል ቡድን ባይሆንም ሊቨርፑል ይህን ጨዋታ እንደሚረታ እገምታለሁ።
ሞሐመድ ሳላህ በዚህ ጨዋታ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ግልፅ ነው።
ግምት፡ 1 - 2
ቶተንሀም ከሳውዝአምፕተን
ሳውዝአምፕተን ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ያገኛል የሚል ግምት የለኝም።
ቶተንሀም ከገና በፊት ወደ ሳውዝአምፕተን ሜዳ ተጉዞ 5-0 አሸንፎ ተመልሷል። የአንጅ ፖስቴኮግሉ ቡድን ጥሩ አቋም ላይ ባይገኝም ይህን ጨዋታ ማሸነፍ አይከብደውም።
ቶተንሀም ጎል ማስቆጠር የተሳነው ይመስላል። ይህን ጨዋታ ግን ተደላድሎ ያሸንፋል።
ግምት፡ 3 - 0

ማንቸስተር ዩናይትድ ከማንቸስተር ሲቲ
ማንቸስተር ዩናይትድ ጎል ማስቆጠር አልቻለም። ሩበን አሞሪም በራስመስ ሆይሉንድ ቦታ ጆሽዋ ዚርክዚ ለምን እንዳሰለፈ አልገባኝም።
ሰዎች ዩናይትድ ከኖቲንግሀም ጋር በነበረው ጨዋታ ጥሩ ነበር ይላሉ። ነገር ግን ጎል ካላስቆጠሩ ጥሩ ቢጫወቱ ዋጋ የለውም።
ኧርሊንግ ሀላንድ በጉዳት በማይሰለፍበት ጨዋታ ሲቲ ጎል መፍጠር እንደሚሳነው ግልፅ ነው። ሲቲ በያዝነው የውድድር ዘመን እንደቀድሞው አስፈሪ አይደለም።
አሞሪም ለሶስተኛ ጊዜ ፔፕ ጉዋርዲዮላን የሚያሸንፉ ከሆነ ትልቅ ድል ነው። ነገር ግን ይህ ይሆናል የሚል ግምት የለኝም።
ግምት፡ 1 - 2
ሰኞ
ሌስተር ከኒውካስል
ሌስተር በኤቲሀድ ያሳዩት አቋም የቀሩት ጨዋታዎችን ሳይጫወቱ ወደታችኛው ሊግ እንዲወርዱ የሚያስደርግ ነው።
ሲቲ 2-0 እየመራ ሌስተር ወደፊት ሄደው ጎል ለማስቆጠር ሙከራ ሲያደርጉ አይታዩም። አቋማቸው እጅግ ደካማ ነበር።
በዚህኛውም ጨዋታ ተመሳሳይ ነገር እናያለን የሚል ግምት አለኝ። ኒውካስል በሳምንቱ አጋማሽ ብሬንትፈርድ መርታት ችሏል።
ከሌስተር ሲቲ ጋር የሚያደርጉትንም ጨዋታ በድል እንደሚወጡት አስባለሁ።
ግምት፡ 0 - 2












