ከእስረኛነት ወደ ፕሬዝዳንትነት የመጡት አዲሱ የማዳጋስካር ወታደራዊ መሪ ማን ናቸው?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ከአንድ ሳምንት በፊት በማዳጋስካር ጎዳናዎች እየተዘዋወሩ ስለ ኮሎኔል ማይክል ራንድሪናሪራ ቢጠይቁ የሚያውቃቸው ሰው ለማግኘት ይቸገራሉ።

በሦስት ቀናት ውስጥ ስማቸው በማዳጋስካር ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚነሳ ሰው ሆነዋል።

በአገሪቱ ኃያሉ ሰው የሆኑትም በሦስት ቀናት ውስጥ ነው።

የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆሊና 'ደኅንነቱ ወደተጠበቀ ሥፍራ' መወሰዳቸውን ተከትሎ ወታደራዊ መኰንኖች የአገሪቱን የመሪነት ሥልጣን ይዘዋል።

ኮሎኔል ማይክል ራንድሪናሪራ በማዳጋስካር ጦር ኃይል ውስጥ ጠንካራ የሚባለው ወታደራዊ ክንፍ መሪ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

የመሪነት መንበሩን ከጨበጡ በኋላ ከቤተ መንግሥት መግለጫ የሰጡት ኮሎኔል ማይክል ራንድሪናሪራ ወታደራዊ መኰንኖች መንግሥት እንደሚያቋቁሙ እና በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ምርጫ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ኮሎኔሉ የአፍሪካ ትልቋ ደሴት ወደ ሆነችው ማዳጋስካር የሥልጣን ማማ ላይ መውጣት የጀመሩት ባለፈው እሑድ ላይ ነው።

የሚመሩት ወታደራዊ ክንፍ ወደ ማዳጋስካር መዲና አንታናናሪቮ አቅንቶ ሥልጣን ተቆጣጥሯል።

በመዲናዋም የወታደሩን እርምጃ በመደገፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ሰንደቅ አላማ ሲያውለበልቡ ታይተዋል።

ወታደራዊው ክንፍ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የፕሬዝዳንቱ ደጋፊ ነበር። ከሰሞኑ ግን የወጣቶችን ተቃውሞ በመደግፍ ወደ ሥልጣን መጥቷል።

ወጣቶች ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን እንዲለቁ በመጠየቅ ለሳምንታት በአደባባይ ተቃውሞ አሰምተዋል።

የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆሊና አገር ጥለው ሸሽተዋል።

የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ፕሬዝዳንቱ በፌስቡክ ባስተላለፉት መልዕክት "የወታደራዊ መኰንኖች እና የፖለቲከኞች ቡድን እኔን ለመግደል አሲረዋል" ማለታቸው አይዘነጋም።

ከአገር ከወጡ በኋላ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የሕዝብ እንደራሴዎች ውሳኔ አሳልፈዋል።

ለሳምንታት በቀጠለው የወጣቶች ተቃውሞ ወደ ሥልጣን የመጡት ወታደራዊ መኰንኖች "ንቅናቄውን የጀመሩት ወጣቶች ስለሆኑ ፍላጎታቸውን እናሟላለን" ብለዋል።

ተቃዋሚዎች እና ወታደሮች ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን ገሸሽ በመደረጋቸው ደስታቸውን እየገለጹ ነው።

የ51 ዓመቱ ኮሎኔል ማይክል ራንድሪናሪራ ሥልጣን መረከባቸውን ካሳወቁ በኋላ በማዳጋስካር ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት የአገሪቱ አዲሱ መሪ ተብለው ተሰይመዋል።

አንድሪ ራጆሊና አሁንም የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት እሳቸው መሆናቸውን ይናገራሉ።

ኮሎኔል ማይክል ራንድሪናሪራ ምሥጢራዊ ሰው ናቸው። የአገሪቱ ጠንካራ ወታደራዊ ክንፍ መሪ ሆነው ነው ወደ ሥልጣን የመጡት።

ስለ እሳቸው በሕዝብ ዘንድ እምብዛም ዝርዝር መረጃ የለም።

የተወለዱት በአገሪቱ ደቡባዊ አንዶሪ ግዛት ሲቮሂፖቲ በተባለ መንደር ነው።

ከአውሮፓውያኑ 2016 እስከ 2018 የአንዶሪ አገረ ገዢ ሆነው አገልግለዋል። በወቅቱ የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት ሔሪ ራጃናሪማምፒና ነበሩ።

ከዚያም እስከ 2022 ድረስ የቶሊራ ከተማ ወታደራዊ ዕዝ ኃላፊ ሆነዋል።

በአንድ ወቅት የአንድሪ ራጆሊና ተቺ ነበሩ።

ከሥልጣን በወጣቶች አመጽ የተባረሩት ነጋዴ እና ዲጄ የነበሩት አንድሪ ራጆሊና በአንድ ወቅት የአገሪቱ ተስፋ ተደርገው ይታዩ ነበር።

በ34 ዓመታቸው ሥልጣን ሲይዙ የአፍሪካ ወጣቱ መሪ ተብለውም ነበር። ለአራት ዓመታት አገሪቱን ከመሩ በኋላ በአውሮፓውያኑ 2018 በድጋሚ ወደ ሥልጣን ተመልሰዋል።

በ2023 ኮሎኔል ማይክል ራንድሪናሪራ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት ማረሚያ ቤት ታስረዋል።

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድርገዋል በሚል ተከሰው ነበር የታሰሩት።

የተማሪዎች ማኅበራት፣ ወታደሮች እና ፖለቲከኞች ኮሎኔል ማይክል ራንድሪናሪራ መታሰራቸውን ተቃውመዋል።

ለእስር የበቁት በሐሰተኛ እና የፖለቲካ ዓላማ ባለው መመሳጠር ነው ብለውም ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ከእስር የተለቀቁት በ2024 ነበር።

ኮሎኔሉ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዷል የሚለውን ባይቀበሉም የአገሪቱ አዲስ መሪ ተብለው ተሰይመዋል።

ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ማዳጋስካር ፕሬዝዳንት ስለሌላት ቀውስ ውስጥ ናት" ብለዋል።

"እኔ የሕዝብ አገልጋይ ነኝ" ሲሉም በትህትና እንጂ በመታበይ ወደ ሥልጣን እንዳልመጡ ተናግረዋል።

ኮሎኔሉ ጠንካራ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ናቸው።

የአገሪቱ ጋዜጠኛ ሪቮኖላ ራዛፊሰን "ቀላል ግን ጠንካራ ሰው ነው። ቀጥተኛ እና አገር ወዳድም ነው" ሲል ይገልጻቸዋል።

ማዳጋስካር አሁንም ድረስ በቀድሞ ቅኝ ገዢዋ በፈረንሳይ ጫና ሥር መሆኗን ይነቅፋሉ።

እስከ 1960ዎቹ ድረስ ማዳጋስካር ከፈረንሳይ ነፃነቷን ሳታገኝ ቆይታለች።

ኮሎኔሉ ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ በፈረንሳይኛ ምላሽ መስጠት ይመርጡ እንደሆነ ተጠይቀው "ለምን በአገሬ ቋንቋ አልናገርም? የቅኝ ገዢን ቋንቋ መጠቀም አልፈልግም" ብለዋል።

ከአገር የሸሹት ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆሊና የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው በኋላ በፈረንሳይ ወታደራዊ አውሮፕላን ከአገር እንደወጡ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የውሃ እና መብራት መቆራረጥን በመቃወም አደባባይ የወጡት ወጣቶች ተቃውሞውን አቀጣጥለው ገፍተውበታል።

ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ሥልጣን በመስጠት እና በሙስና የሚከሰሱት አንድሪ ራጆሊና ከወጣቶች ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

የወጣቶች የአደባባይ ተቃውሞ ሳይባባስ በፊት ፕሬዝዳንቱ መንግሥታቸውን በትነዋል።

የራሳቸውን ፓርቲ አባላት ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች ፕሬዝዳንቱ እንዲከሰሱ ድምጽ ሰጥተዋል።

ሥራ አጥነት፣ ሙስና እና የኑሮ ውድነት ዋነኛ የተቃውሞው ማጠንጠኛ ናቸው። ሰልፈኞች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው ቢያንስ 22 ሰዎች ሲገደሉ 100 የሚደርሱ እንደተጎዱ የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል።

የማዳጋስካር መንግሥት የተገለጸው ቁጥር "ሐሰተኛ ነው" ብሏል።

አዲሱ ተሿሚ ለማዳጋስካር መገናኛ ብዙኃን እንዳሉት ዋነኛ ትኩረታቸው የኅብረተሰቡን የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው።

ከማዳጋስካር 30 ሚሊዮን ሕዝብ 75 በመቶ የሚሆነው ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖር የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል።

ኮሎኔል ማይክል ራንድሪናሪራ እንዳሉት፤ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ ምርጫ ይካሄዳል። እስከዚያ ድረስ አገሪቱ በወታደራዊ መኰንኖች ትመራለች።

የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ሥልጣን መቆጣጠሩን ካሳወቀ ከጥቂት ቀናት በኋላ ኮሎኔሉ አርብ ዕለት ቃለ መሐላ ፈጽመው በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የምትገኘው አፍሪካዊት አገር አዲስ ፕሬዝዳንት በመሆን በይፋ ሥልጣን ተረክበዋል።

በቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ የተካሄደውን ዓመጽ የመሩት ተቃዋሚዎችን ጨምሮ በርካታ ሕዝብ በዋና ከተማዋ በሚገኘው ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ውስጥ ተገኝነተው ነበር።

ኮሎኔል ማይክል ራንድሪናሪራ ቃለ መሐላ ፈጽመው የማዳጋስካር መሪነትን መረከባቸውን ተከትሎ አገሪቱ ከተቃውሞ ወጥታ ወደ ሽግግር ገብታለች።

የቀድሞውን መሪ ከአገር ያስወጣውን ተቃውሞ ያካሄዱት ወጣቶች እና ቀሪው የማዳጋስካር ሕዝብ አዲሱ ፕሬዝዳንት ከመንግሥታቸው የሚጠብቋቸውን ተግባራት ይፈጽማሉ ብለው ተስፋ አድርገዋል።