በአርሜኒያ እና አዘርባጃን መካከል በተቀሰቀሰ አዲስ ግጭት በርካቶች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአጎራባቾቹ አርሜኒያ እና አዘርባጃን መካከል በተከሰተ አዲስ የድንበር ግጭት በርካታ ወታደሮች መገደላቸው ተገለጸ።
የአርሜኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮላ ፓሺንያን ማክሰኞ መስከረም 03/2015 ዓ.ም. ሌሊት ላይ ባጋጠመው ግጭት 49 የአገሪቱ ሠራዊት አባላት መገደላቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ በጠላትነት የሚተያዩት ጎረቤት አገራት ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ሁለት ጊዜ ጦርነት የገጠሙ ሲሆን አነስተኛ የሆኑ ግጭቶች ግን በተደጋጋሚ ይከሰታሉ።
በቅርቡ ተካሂዶ የነበረው ጦርነት በተኩስ አቁም ስምምነት እንዲጠናቀቅ ማድረጓን ሩሲያ ብትገልጽም፣ አርሜኒያ ግን ግጭቱ ለጊዜው ጋብ ብሎ ቆየ እንጂ ጦርነት ሙሉ በሙሉ አልቆመም ትላለች።
አርሜኒያ እና አዘርባጃን በተደጋጋሚ ለግጭት የሚዳርጋቸው ናጎረኖ-ካራባክህ በተባለው የድንበር አካባቢ በሚያነሱት የይገባኛል ጥያቄ ነው።
በዚህ አወዛጋቢ አካባቢ ዓለም እውቅና የሰጠው ለአዘርባጃን ይሁን እንጂ አብዛኛው ነዋሪ ግን አርሜናዊያን ናቸው።
ሁለቱ ጎረቤት አገራት ልዩነታቸው ፖለቲካ ብቻ አይደለም። አብዛኛው የአርሜኒያ ዜጋ የክርስትና እምነት ተከታይ ሲሆን፣ በተቃራኒው ከአዘርባጃን ሕዝብ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ሙስሊሙ ማኅብረሰብ ነው።
ሁለቱ አገራት እአአ በ1980ዎቹ እና በ1990ዎቹ ወደለየለት ጦርነት ገብተው ነበር። እአአ 2020 ደግሞ ለስድስት ሳምንታት የዘለቀ ደም አፋሳሽ ጦርነት አካሂደው ነበር።
ሰኞ ምሽት ተቀስቅሶ ለበርካታ ወታደሮች ሞት ምክንያት ለሆነው ግጭት አንዳቸው ሌላኛውን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
አርሜኒያ አዋሳኝ ድንበር ላይ የሚገኙ ከተሞቿ በአዘርባጃን ከባድ መሳሪያ ከተደበደቡ በኋላ፣ የአጸፋ ምላሽ መስጠቷን ትገልጻለች።
አዘርባጃን በበኩሏ ወታደራዊ እርምጃ የወሰደችው ጦሯ ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ መሆኑን ትናገራለች።
ሞስኮ ማክሰኞ ንጋት ላይ ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ከማደራደሯ በፊት ሌሊቱን ሙሉ በሁለቱ አገራት ወታደሮች መካከል የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ እንደነበረ ተገልጿል።
የአርሜኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሺንያን ግን አዘርባጃን በአንድ ወይም ሁለት ግንባር ጥቃት ማድረሷን እንደቀጠለች ነው ይላሉ።
ሰኞ ምሽት ተከስቷል በተባለው ግጭት በአዘርባጃን ጦር ላይ ጉዳት ስለመድረሱ ተገልጿል። የአገሪቱ ጦር እስካሁን በግጭቱ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ እና እንደቆሰሉ ያለው ነገር የለም።
የግጭቱን መቀስቀስ ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ አጥብቆ ኮንኗል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ “ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሄ የለም” ብለዋል።
ለአርሜኒያ ታሪካዊ ቅርበት ያላት ሩሲያ አሁን ላይ ያለው አለመግባባት መቀረፍ ያለበት “በፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ” መንገድ መሆን አለበት ብላለች።
ሞስኮ ሁለቱም አገራት ራሳቸውን ከግጭት እንዲያቅቡ አሳስባለች።
ለአዘርባጃን የምትወግነው ቱርክ ደግሞ አርሜኒያ ከጠብ ጫሪነት እራሷን መግታት አለባት ብላለች። የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማቭሉት ቻቩሾሎ፤ “አርሜኒያ ግጭት ከመቀስቀስ ታቅባ ትኩረቷን የሰላም ንግግር ላይ ማድረግ አለባት” ብለዋል።
ሰኞ ምሽት ያጋጠመው ግጭት ከእአአ 2020 ጦርነት በኋላ የከፋው ነው ተብሏል። ከሁለት ዓመት በፊት በነበረ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሁለቱም ወገን ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ጦርነቱ በአዘርባጃን አሸናፊነት እንደተጠናቀቀ ይታሰባል።
ሞስኮ የጦርነቱን ተሳታፊዎች ካሸማገለች በኋላ አርሜኒያ ከናጎርኖ-ካራባክሃ ግዛት ጦሯን ለማስወጣት ተገዳ ነበር።
በድርድሩ ስምምነት መሠረት አርሜኒያ እና አዘርባጃን ይገባኛል በሚሉት አካባቢ ሞስኮ 2ሺህ አባላት ያሉት ሰላም አስከባሪ ጦር ያሰማራች ሲሆን፣ ይህ ጦር አሁንም በስፍራው ተሰማርቶ ይገኛል።












