አርብቶ አደሮችን ሰብስቦ የሚያስተምረው የ11ኛ ክፍል ኢትዮጵያዊ ተማሪ

ሳሮ ገልገሎ ይባላል።
ተወልዶ ያደገው በኦሮሚያ ቦረና ዞን፣ መታ ወያማ ወረዳ፣ መታ አርባ ቀበሌ ሲሆን በቦርቦር መሰናዶ ትምህርት ቤት ውስጥ የ11ኛ ክፍለ ተማሪ ነው።
ዘወትር ቅዳሜ ከሚማርበት ትምህርት ቤት ቤተሰቦቹ የሚገኙበት ለመሄድ 43 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠበቅበታል።
ቤተሰቦቹ የሚኖሩት መታ አርባ በሚባል መንደር ነው።
መታ አርባ፣ በመታ ወያማ ወረዳ ውስጥ የምትገኝ አነስተኛ መንደር ናት።
ሳሮ ዘወትር ወደ ቤተሰቦቹ ጋር ሲሄድ የመንደሪቷ ነዋሪዎች ከስልካቸው ውስጥ የሚፈልጉትን ቁጥር አውጥተው መደወል ሲቸገሩ ያስተውላል።
ይህ ብቻም ሳይሆን ለእረፍት ቤተሰቦቹ ጋር በሚያሳልፍበት ቅዳሜ እና እሁድ የመንደሪቷ ነዋሪዎች ስልካቸውን ይዘው ወደ እርሱ እየመጡ ወደሚፈልጉት ሰው እንዲደውልላቸው ይጠይቃሉ።
ይሄኔ “እኔ ወደዚህች መንደር የምመጣው በሳምንት ሁለቴ፤ ታድያ ለምን እኔ በሌለሁበትም ጊዜ ቢሆን ራሳቸው አንብበው ቢያንስ ስልክ መደወል እንዲችሉ አላደርግም” ሲል አሰበ።
ይህንንም ሃሳብ ለአካባቢው ነዋሪዎች ሲያካፍላቸው ተስማሙ።
“የአካባቢው ማህበረሰብ ለትምህርት ጉጉት አለው። በማስተምራቸውም ጊዜ በተቻለ መጠን በንቃት ይሳተፋሉ” ይላል።

ሳሮ ማስተማር በጀመረበት ዓመት በአካባቢው የሚገኝ አነስተኛ ትምህርት ቤትን መጠቀም ችሎ ነበር።
ነገር ግን በአካባቢው በተከሰተ ድርቅ ምክንያት ነዋሪዎቹ ወደ ሌላ ስፍራ ተሰደዱ።
ይህ ግን የተነሳበትን ዓላማ አላጨናገፈውም። የመንደሪቷ ነዋሪዎች ተፈናቅለው በሚኖሩበት አካባቢ ሰብስቧቸው ማስተማሩን ቀጠለ።
ሳሮ እስካሁን ድረስ የአካባቢውን ነዋሪዎች ከሶስት ዓመት በላይ አስተምሯል።
ትምህርት በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ በነበረበት ወቅትም እሱ ማስተማር መቀጠሉን ይናገራሉ።
“ትምህርት ቤት በሚዘጋበት ወቅት ወደ መንደሬ ሄጄ ነዋሪዎቹን ዛፍ ጥላ ስር በመሰብሰብ አስተምራቸዋለሁ”
እስካሁን ድረስ ከ94 በላይ ጎልማሶችን፣ 123 ደግሞ እድሜያቸው ከ5 እስከ 30 የሚሆን ተማሪዎችን ፊደል አስቆጥሯል።
ሳሮ ተማሪዎቹ ቢያንስ መሰረታዊ ፊደል መለየት እንዲችሉ አድርጓል። ከዚያም አለፍ ሲል ቀላል የሂሳብ ስሌቶችን መስራት እንዲችሉ አስተምሯቸዋል።
በዚህ ዓመት ይላል ሳሮ እርሱ ጋር ለመማር 112 አዲስ ተማሪዎች ተመዝግበዋል።
ሳሮ ዋቆ ዘጠኝ ለወለዱ ቤተሰቦቹ ሰባተኛ ልጅ ነው።
ከቤተሰቦቹ መካከልም ወደ ትምህርት ቤት መሄድ የቻለው እርሱ ብቻ ነው።
የአርብቶ አደር ልጅ የሆነው ሳሮ፣ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል።
በአካባቢው በተደጋጋሚ በሚከሰት ድርቅ ምክንያት ከትምህርት ገበታው ሊስተጓጎል የሚችልባቸው ምክንያቶች ተፈጥረውም እንደነበር ይናገራል።
“ቤተሰበቦቼ በድርቅ ምክንያት ያላቸውን ሁሉ ሲያጡ ራሴን ለማስተማር ወሰንኩ። ቦርቦር ከተማ ወደ ሚገኙ ዘመዶቻችን ዘንድ ሄጄ ትምህርቴን ቀጠልኩ” ይላል።
የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ሞተር ብስክሌት መንዳት መማሩን የሚናገረው ሳሮ፣ ስራ እየሰራ እስከ ሰባተኛ ድረስ ትምህቱን መግፋቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።
የ60 ዓመቷ ሎኮ ሳራ ዋቆ፣ የስምንት ልጆች እናት ሲሆኑ ለሶስት ወራት ያህል ሳሮ ማንበብና መጻፍ እንዳስተማራቸው ይናገራሉ።
“አራት ልጆቼን ጨምሬ እያስተማርኩ ነው። ከስልኬ ውስጥ ስምንና ስልክ ለይቼ ማውጣት አልችልም ነበር። ከተደወለልኝም ሁሌ ማን እንደሆነ ጠይቄ ነበር የምረዳው፤ አሁነ ግን ራሴ ስልኮችን መጻፍ፣ አንብቤ መለየት እችላለሁ” በማለት ሳሮን ያመሰግናሉ።

አቶ ጃተኒ ሶራም እንዲሁ የ50 ዓመት ጎልማሳ ናቸው።
በየእለቱ ከእርሳቸው ጋር አብረው የሚማሩ 41 ሰዎች መኖራቸውን ይናገራሉ።
ለእነዚህ ሁሉ ተማሪዎች ግን ያላቸው አንድ መምህር ብቻ መሆኑ ጥያቄ ይፈጥርባቸዋል። በዚያ ላይ አዲሱ የትምህርት ዘመን ሲከፈት ወደ ከተማ ተመልሶ ስለሚሄድ ትምህርታቸው ይስተጓጎላል ብለው ሰግተዋል።
የቀለምን ጣዕም አውቀው፣ የእውቀት ብርሃን በርቶላቸው ዳግም ማቋረጥ አልፈለጉም።
በስልካቸው ውስጥ ያለን ቁጥር እና ስም እንዲያነቡ ለማስቻል የተጀመረው ማስተማር ዛሬ በርካቶችን ትምህርት እንዲወዱ እና የበለጠ መማር እንዲፈልጉ ማድረጉን ሳሮም ይናገራል።
ቢቢሲ ለሳሮ መምህር የመሆን ፍላጎት አለህ ሲል ጥያቄ አቅርቦለት ነበር።
“በጭራሽ” ነበር መልሱ። መምህርነትን የሚጠላው ሙያ ሆኖ ሳይሆን ማጥናት የሚፈልገው የሕዝብ አስተዳደር መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።
ምንም እንኳ አዲሱ የትምህርት ዘመን ሲጀምር ወደ ቦርቦር ከተማ ሄዶ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን መቀጠል ቢኖርበትም እዚህ መንደሩ ውስጥ የሚያስተምራቸው ሰዎች ሁኔታም ያሳስበዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም ይህንን ስለሚረዱ ሌላ መምህር መድቦላቸው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የአካባቢውን አስተዳደር መጠየቃቸውን ገልፀዋል።












