የአሜሪካ ፍርድ ቤት በማቀዝቀዣ የሚቀመጡ ሽሎች እንደ ሕጻን ይቆጠራሉ ማለቱ ውዝግብ ፈጠረ

የፎቶው ባለመብት, CARLOS DUARTE
የአላባማ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በማቀዝቀዣ ውስጥ ያሉ ሽሎች እንደ ሕጻናት ስለሚቆጠሩ እነሱን እነሱን ባጋጣሚም ቢሆን ያበላሸ በሕግ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል ማለቱን ተከትሎ በአሜሪካ የሥነ ተዋልዶ ጤና ሕክምና ጋር በተያያዘ አዲስ ውዝግብ ተፈጠረ።
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎም በወንጀል ክስ ተጠያቂ ሊያደርግ ይችላል በሚል በደቡባዊቷ የአሜሪካ ግዛት የሚገኘው ትልቅ ሆስፒታል የሚሰጠውን በቴክኖሎጂ የታገዘ የመካንነት ሕክምና ዘዴ (IVF) አገልግሎቱን አቋርጧል።
አይቪኤፍ ከሴቷ እንቁላል ከወንዱ ደግሞ የዘር ፈሳሽ በመውሰድ በቤተ ሙከራ እንዲገናኙ ተደርጎ ፅንስ ከተፈጠረ በኋላ ያ ፅንስ ተመልሶ ማህፀን ውስጥ እንዲገባና ፅንሱ በእናቱ ማህጸን እንዲያድግ የሚደረግበት የሕክምና ሒደት ነው።
ሆኖም የአላባማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ፣ ከሴቶች የእንቁላል ማምረቻ ቱቦ እንቁላል ማውጣቱን ሊቀጥል እንደሚችል፤ ነገር ግን ቀጣይ ሒደት የሆነውን የአይቪኤፍ ሕክምናውን እንደሚያቆም ገልጿል።
“ ይህ ውሳኔ በአይቪኤፍ አማካኝነት ልጅ ለማግኘት እየሞከሩ ያሉ ታካሚዎቻችንን የሚጎዳ በመሆኑ እናዝናለን” ብሏል ሆስፒታሉ በመግለጫው።
“ ሆኖም ታካሚዎቻችን እና ሐኪሞቻችን በወንጀል ሊከሰሱ የሚችሉበትን ዕድል አሊያም የሕክምናውን ሒደት በመከተል ሊደርስባቸው የሚችለውን ጉዳት መገምገም አለብን” ብሏል።
የሕክምና ባለሙያዎች እና የሥነ ተዋልዶ ጤና ተሟጋች ቡድኖች በበኩላቸው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በአላባማ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ያለው የመካንነት ሕክምና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያስከትላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ወግ አጥባቂ ቡድኖች በበኩላቸው “ ሽልም ሕጋዊ ጥበቃ” ያስፈልገዋል ሲሉ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በበጎ ተቀብለውታል።
ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 ሦስት ጥንዶች የመካንነት ሕክምና በሚሰጥበት ሆስፒታሉ ያስቀመጧቸው ሽሎች 'በግድየለሽነት' ሞተዋል ሲሉ ክስ ካቀረቡ በኋላ ነበር።
አንድ ታካሚ ሽሎቹን ከተቀመጡበት ቦታ ስታነሳ በድንገት ከወደቁባት በኋላ ነበር ክስተቱ ያጋጠመው።
ከዚያም ጥንዶቹ የሥነ ተዋልዶ ሕክምና ማዕከሉና በአላባማ መንግሥታዊ ባልሆነው ሞባይል ኢንፍርማሪ ማኅበር ላይ ባልተወለዱ ሕጻናት ሞት ክስ ያቀርባሉ።
ያልተወለዱ ሕጻናትን የሚመለከተው ሕግ ፅንስን የሚመለከት ቢሆንም በአይቪኤፍ የተብላሉ ሽሎችን በተመለከተ ግን በዝርዝር የሚለው ነገር የለም።
ጥንዶቹ ክሱን የመሰረቱበት የሥር ፍርድ ቤቱም “ ሽሉ እንደ ሰው አሊያም ሕጻን አይቆጠርም” በማለት የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርጎት ነበር።
ነገር ግን ይግባኝ የጠየቁበት የአላባማ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን ከጥንዶቹ ጎን በመቆም በማቀዝቀዣ ውስጥ ያሉ ሽሎች አንደ ሕጻን እንዲቆጠሩ ውሳኔውን አሳልፏል።
ሽሎቹ የተቀመጡት በማቀዝቀዣም ይሁን በማህጸን 'በግድየለሽነት የሚከሰትን ሞት' የሚመለከተው የግዛቷ ሕግ ሁሉንም ያልተወለዱ ሕጻናትን እንደሚመለከትም ፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ዋና ዳኛ የሆኑት ቶም ፓርከር “ ከመወለድ በፊት ሁሉም ሰው የፈጣሪ አምሳያ አለው። በመሆኑም ያለ እሱ ፈቃድ ሕይወታቸው ማለፍ የለበትም” ብለዋል።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አይቪኤፍን አይከለክልም አሊያም አይገድብም። ሆኖም የተወሰኑ የሕክምናው ክፍሎች በአላባማ ሕግ፣ ሕጋዊ መሆን አለመሆናቸው ግርታዎችን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ሽል እንደ ሰው የሚቆጠር ከሆነ ክሊኒኮች እንዴት መሥራት እና ማከማቸት እንደሚፈቀድላቸውም ጥያቄዎችን ሊያስነሳ ይችላል።
በሥነ ተዋልዶ ጤና መብት የፖሊሲ ዳይሬክተር የሆኑት ኤልዛቤት ስሚዝ ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ “ሁሉም ሽሎች ጥቅም ላይ አይውሉም። በመሆኑም ሽሎችን እንደ ሰው የምንቆጥር ከሆነ በርካታ ሰዎች ቤተሰብ እንዲኖራቸው በሚጠቀሙት የህክምና ዘዴ አይቪኤፍ ጥቅም ላይ ከባድ ተፅዕኖ ያስከትላል” ብለዋል።
ሕክምናው ይቀጥላል አይቀጥልም ፤ ሕጋዊ ነው አይደለም በሚል በሕጉ ላይ የተፈጠረው ብዥታ በታካሚዎቹም ላይ ተጋብቷል።
በአላባማ ግዛት የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ባወጣው መግለጫም ውሳኔው የሕክምና ዘዴውን በመጠቀም ቤተሰብ እንዲኖራቸው የሚፈልጉ የአላባማ ነዋሪዎችን የሚጎዳ ሲሆን ጥቂት ልጆች፣ የልጅ ልጆች፣ የእህት ልጆች፣ የወንድም ልጆች. . . እንዲኖራቸው ያደርጋል” ብሏል።
እንደ የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል መረጃ ከሆነ እንደ አውሮፓውያኑ 2021 በአይቪኤፍ ሕክምና 97 ሺህ 128 ሕጻናት ተወልደዋል።












