በአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ግዛት ሦስት ዋናተኞች በአሳ ነባሪ ጥቃት ደረሰባቸው

የፎቶው ባለመብት, South Walton Fire District
በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት ሦስት ዋናተኞች በሁለት የተለያዩ ጊዜያት በአሳ ነባሪ ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ወደ ባህር ዳርቻ ለመዝናናት የሚሄዱ ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልዕክት ተላለፈ።
በሰሜን ምዕራብ ፍሎሪዳ ዋልተን አውራጃ አንዲት ሴት አርብ ዕለት በሻርክ ከተነከሰች በኋላ የአንድ እጇ የተወሰነው ክፍል መቆረጡ ተነግሯል።
ሁለት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ የባህር ዳርቻ፣ ሁለት ልጃገረዶች በአሳ ነባሪ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተነግሯል።
አንደኛዋ "በላይኛው እግሯ እና በአንድ እጇ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል" የተባለ ሲሆን ሁለተኛዋ ደግሞ በአንደኛው እግሯ ላይ ቀላል ጉዳት እንደደረሰባት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተናግረዋል።
ባለሥልጣናት የባህር ዳርቻውን በጀልባዎች እየጠበቁ ሲሆን አንዳንድ የባህር ዳርቻዎችም ተዘግተዋል። ምንም እንኳን የባህር ዳርቻዎቹ ቅዳሜ ዕለት እንደገና ቢከፈቱም አደገኛ የአሳ ነባሪ ጥቃት ሊኖር እንደሚችል የሚያስጠነቅቅ ምልክት ተቀምጧል።
የመጀመሪያው ጥቃት የደረሰው አርብ ግንቦት 30/2016 ዓ.ም. ሲሆን በአንዲት የ45 ዓመት እንደሆናት በምትገመት ሴት ላይ በወተርሳውንድ ቢች አቅራቢያ መሆኑ ተነግሯል።
በዳሌዋ እና በታችኛው የግራ እጇ ላይ “ከባድ ጉዳት” ደርሶባት በሄሊኮፕተር ወደ ሆስፒታል ተወስዳለች ሲሉ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተናግረዋል።
የአደጋ ጊዜ ኃላፊ የሆኑት ሪያን ክራውፎርድ የእጆቿ ክፍል መቆረጥ ግድ ሆኗል ማለታቸውን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግበዋል።
ሁለተኛው ጥቃት 15 ዓመት እንደሆናቸው በሚገመቱ ሁለት ልጃገረዶች ላይ በሴክረስት ቢች አቅራቢያ መድረሱ ተገልጿል።
"እባክዎ በጥንቃቄ ይዋኙ። . . . ለሚወዷቸው ሰዎች ይጠንቀቁ" ሲል የደቡብ ዋልተን የእሳት አደጋ በኤክስ ገጹ ላይ አስፍሯል።

የፎቶው ባለመብት, South Walton Fire District
የዋልተን ካውንቲ የፖሊስ ጽህፈት ቤት ትናንት ቅዳሜ ሰኔ 1/2016 ዓ.ም. በኤክስ ላይ እንዳሰፈረው ከሆነ በቅኝት ወቅት በሳንታ ሮሳ ባህር ዳርቻ 4.2 ሜትር የሚረዝም ሻርክ ቢመለከቱም ይህ ግን “የተለመደ ነው” ሲል አጽንኦት ሰጥቷል።
“ሻርኮች ሁል ጊዜ በባህረ ሰላጤው ውስጥ እንደሚገኙ ደጋግመን መግለጽ እንፈልጋለን።”
"ዋናተኞች እና ወደ ባህር ዳርቻዎች ለመዝናናት የሚሄዱ ሰዎች ሁሌም ጥንቃቄ ማድረግ እና አካባቢያቸውን ማወቅ አለባቸው።”
እንደ የፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የሻርክ ጥቃት (አይኤስኤፍ) መረጃ ከሆነ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ70 እስከ 100 የሚደርሱ የሻርክ ጥቃቶች የሚፈጸሙ ሲሆን ወደ አምስት የሚጠጉ ሰዎችም ህይወታቸው ያልፋል።
በፍሎሪዳ፣ አብዛኛው የአሳ ነባሪ ጥቃት የሚፈጸመው በሪኪዊም በሚባሉ አሳ ነባሪዎች ነው ተብሏል።
አብዛኛዎቹ ጥቃቶች የሚፈጸሙት በባህር ዳርቻ ውሃዎች አካባቢ ነው።












