በትግራይ አዲ ዳዕሮ ዳግም ተፈጸመ በተባለ የአየር ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

ማክሰኞ መስከረም 24/2015ዓ.ም. ትግራይ ውስጥ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን በስፋራው ያሉ የረድኤት ድርጅት ሠራተኛ ለቢቢሲ ተናገሩ።
የአየር ጥቃቱን በተመለከተ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ትናንት በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አዲ ዳዕሮ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ፈጸሙን ገልጸው ነበር።
ለዚህ የአየር ጥቃትም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ አየር ኃይሎች ተጠያቂ ናቸው ሲሉ ቢከሱም፣ ከሁለቱም አገራት በኩል ስለጥቃቱ የተባለ ነገር የለም።
ቃል አቀባዩ ጨምረው እንደገለጹት የሰው አልባ አየር ጥቃቱ የተፈጸመው ጦርነት ሸሽተው በመጠለያ ጣቢያ በሚገኙ ሰዎች ላይ ነው ብለዋል።
አንድ የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኛም በተመሳሳይ የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው ከአዲ ዳዕሮ ወደ ሽረ እንዳ ሥላሴ 5 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ላይ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ እኚህ የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኛ እንደሚሉት ከሆነ በጥቃቱ ከ65 የማያንሱ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከ70 በላይ ሰዎች ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሶባቸዋል።
“የተጎዱ ሰዎች ወደ ሽረ ሆስፒታል ተወስደዋል። የመድኃኒት እና የሕክምና እጥረት ስላለ ሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል” ብለዋል የእርዳታ ድርጅት ሠራተኛው።
በተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ላይ ተፈጽሟል በተባለው የአየር ጥቃት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕጻናት እና አዘውንቶች ጉዳት እንዳጋጠማቸው አቶ ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም ሠራዊቱ የሚፈጽማቸው የአየር ጥቃቶች በጥንቃቄ የተመረጡ እና ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ብቻ ያነጣጠሩ መሆናቸውን ገልጾ ነበር።
በተጨማሪም ሰላማዊ ሰዎች ለጥቃት ተጋላጭ ሊሆኑ ከሚችሉ ወታደራዊ ኢላማዎች እንዲርቁ ማሳሰቢያ መስጠቱ ይታወሳል።
በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ለኤርትራ አዋሳኝ በሆነው ስፍራ መስከረም 24/2015 ዓ.ም. ተፈጽሟል ስለተባለው የአየር ጥቃት የፌደራል መንግሥቱም ይሁን የኤርትራ መንግሥት ያሉት ነገር የለም።
በአካባቢው የግንኙነት መስመሮች ባለመኖራቸው ቢቢሲ ከተጨማሪ ምንጮች ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
ይሁን እንጂ በዚህ አዲ ዳዕሮ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ የአየር ጥቃት ሲፈጸም ግን ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በዚሁ አካባቢ መስከረም 17/2015 ዓ.ም. የአየር ጥቃት መፈጸሙን የትግራይ ኃይሎች ከገለጹ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጦ ነበር።
በወቅቱ መንግሥት የኢትዮጵያ አየር ኃይል “ሰሞኑን በተመረጡ ዒላማዎች ላይ እርምጃ ወስዷል” ቢልም የትግራይ ኃይሎች ግን አዲዳዕሮ ተብላ በምትጠራው እና በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በምትገኘው ከተማ ላይ የአየር ጥቃቱን የፈጸመው ኤርትራ ናት ሲሉ ከሰው ነበር።
መንግሥት መስከረም 17 በተፈጸም የአየር ጥቃት ዒላማ የነበረው ወታደራዊ ቁሳቁሶች እና ተተኳሾች ያሉበትን ቦታ ነው ቢልም የትግራይ አመራሮች ግን በጥቃቱ ዒላማ ተደርገው የተገደሉት ሰላማዊ ሰዎች ናቸው ብለዋል።
በመስከረሙ 17 ጥቃት ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን አንድ የረድዔት ሠራተኛ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
ትናንት መስከረም 25 በተፈጸመው ጥቃት ጉዳት ያጋጠማቸው ሰዎች ለሦስተኛ ዙር ያገረሸውን ጦርነት ሸሽተው በመጠለያ ጣቢያ የነበሩት መሆኑን የተመድ ሠራተኛው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
“ጦርነት እየተካሄድ ከሚገኙባቸው አዲ ሃገራይ፣ ጸሊሞ፣ ደደቢት፣ ሽራሮ እና አስገደ ሸሽተው የመጡ ናቸው። ቢዘህ አካባቢ በሚገኙ ግዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች እስከ 300 ሸህ የሚደርሱ ተፈናቃዮች አሉ” ብለዋል።
ይህ የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኛ እንደሚሉት ከሆነ የአየር ጥቃቱ በተፈመበት አካባቢ ምንም አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ የለም።
ለሦስተኛ ዙር ያገረሸው ጦርነት
ነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም. ላይ የሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ካገረሸ በኋላ በትግራይ እና አዋሳን የአማራ ድንበር አካባቢዎች ከፍተኛ ውጊያ ሲሄድ መቆየቱ ይገለጻል።
የኢትዮጵያ ሠራዊትም በሰው አልባ አውሮፕላኖች በመታገዝ በዋና ከተማዋ መቀለ እና በሌሎች ስፍራዎች ላይ የአየር ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል።
የፌደራል መንግሥት ግን እነዚህ የአየር ጥቃቶች የሚያካሂደው በሲቪሎች ላይ ጉዳት ሳያደርስ በከፍተኛ ጥንቃቄ የወታደራዊ ዒላማዎችን እየነጠለ መሆኑን ይገልጻል።
በተጻራራዊ የትግራይ ኃይሎች የአዲስ አበባ እና የአሥመራ መንግሥታት የሚፈጽሙት የአየር ጥቃቶች ዒላማቸው ንሑሃን ሰዎች ናቸው ይላሉ።
የሰላም ጥረት
ትናንት ተፈጽሟል በተባለው እና በርካታ ሰዎች ተገድለውበታል የተባለው ጥቃት የተሰማው ተዋጊ ኃይሎች በደቡብ አፍሪካ ተገናኝተው ለሰላም ንግግር ሊቀመጡ ይችላሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው።
የፌደራሉን መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ለማደራደር ጥረት እያደረገ ያለው የአፍሪካ ሕብረት የሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች የፊታችን የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ለሰላም ንግግር በደቡብ አፍሪካ እንዲገኙ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ደቡብ አፍሪካ ለሚካሄደው የሰላም ድርድር የቀረበለትን ግብዣ መቀበሉን አስታውቋል።
ይህ የንግግር ጥሪ ለትግራእ ኃይሎችም የቀረበ ሲሆን ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኑ ህወሓቶች ለዚህ የንግግር ጥሪ እስካሁን ምላሽ ስለመስጠታቸው በይፋ የተባለ ነገር የለም።












