በዩናይትድ ኪንግደም መጥፎ የአየር ጸባይ በርካታ በረራዎችን አስተጓጎለ

ታትሟል

በዩናይትድ ኪንግደም መጥፎ የአየር ጸባይ በርካታ የአየር በረራዎችን እና የባቡር ጉዞዎችን አስተጓጎለ።

ከለንደን በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው ስታንስቴድ አየር ማረፊያ በመጥፎ የአየር ሁኔታ የተነሳ መንደርዳሪያዎችን ከዘጋ በኋላ ከአየር ማረፊያው የሚነሱ እና የሚያርፉ አውሮፕላኖች የሉም።

ሌሎቹ እንደ ሂትሮ እና ጋትዊክ ያሉ ግዙፍ አየር ማረፊያዎችም በበረዶ እና በጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ምክንያት በርካታ በረራዎችን ለመሰረዝ እና ለማዘግየት ተገደዋል።

የአገሪቱ መንግሥት በስኮትላንድ፣ ለንደን እና ደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ ‘የቢጫ’ ደረጃ የአየር ሁኔታ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።

‘ቢጫ’ ደረጃ በመጥፎ የአየር ጸባይ ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት ሊስተጓጎል ስለሚችል ሰዎች ቀድመው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያሳስብ ነው።

በአሁኑ ወቅት በዩኬ አንዳንድ አካባቢዎች የቅዝቃዜ ደረጃ ከዜሮ በታች 15 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊደርስ እንደሚችል ዩኬ ሜት አስታውቋል።

የባቡር የትራንስፖርት አማራጮችም በመጥፎ የአየር ሁኔታው መዘግየት አጋጥሟቸዋል። በርካታ የመኪና አደጋ ማጋጠሙን ተከትሎ ደግሞ አሸከርካሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ወጥቷል።

የክረምቱ ወራት መግባትን ተከትሎ የተከሰተው ቀዝቃዛማ የአየር ሁኔታ በትራንስፖርት ዘርፉ ተጨማሪ መስተጓጎሎችን እንደሚያስከትል ተገምቷል።

ስታንስቴድ እሑድ ምሽት ባወጣው መግለጫ ያለውን አንድ የአውሮፕላን መንደርደሪያ ከበረዶ ማጽዳት በማስፈለጉ የሚነሱ እና የሚያርፉ አውሮፕላኖች አይኖሩም ብሏል።

በለንደኑ ትልቁ አየር ማረፊያ ሂትሮ ደግሞ ትናንት እሑድ ከ50 ያላነሱ በረራዎች ተሰርዘዋል።

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በመጥፎ የአየር ጸባይ ምክንያት በአንድ ሰዓት ውስጥ ማስተናገድ የሚችሉት የአውሮፕላን ቁጥር ዝቅ በማለቱ ነው በረራዎች የተሰረዙት።

ብሪቲሽ አየር መንገድ በመጥፎ የአየር ጸባይ ምክንያት በረራቸው የተሰረዘባቸው መንገደኞች በሌላ በረራ ላይ እንዲመዘገቡ አልያም ደግሞ ገንዘብ ተመላሽ እያደርገ መሆኑን አስታውቋል።

በተመሳሳይ በጋትዊክ አየር ማረፊያ በርካታ በረራዎች የተሰረዙ ወይም እንዲዘገዩ የተደረጉ ሲሆን፤ መዳረሻቸውን ለመቀየር የተገደዱ አውሮፕላኖችም አልጠፉም።

የማንችስተር አየር ማረፊያ ደግሞ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ያሉትን ሁለት መንደርደሪያዎች በበረዶ ምክንያት ለመዝጋት ተገዶ ነበር።  

ትናንት በመጥፎ የአየር ጸባይ ምክንያት ያጋጠመው መዘግየት እና የበረራ መሰረዝ ሊቀጥል እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።