ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትዊተር በአፍሪካ ያሉትን ሰራተኞች ቀነሰ
ትዊተር የአፍሪካ ብቸኛ መቀመጫ የሆነው እና በጋና በሚገኘው ቢሮው ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞቹን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ቀነሰ።
ተቐሙ ወጪውን ለመቀነስ በማሰቡ መዋቅሩን በድጋሚ እያጤነ እንደሚገኝ የሚገልጽ ኤሜይል ለሰራተኞቹ የላከ ሲሆን ቢቢሲም ኢሜይሉን ተመልክቷል።
ትዊተርን በቅርቡ የገዛው ባለቤቱ ኤሎን መስክ በአለማቀፍ ደረጃ የሰራተኛ ቅነሳ እንዲደረግ መወሰኑ ይታወሳል።
የጋናው ቢሮ ባለፈው አመት የተከፈተ ሲሆን ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴው በአፍሪካ ውስጥ ባሉ ውይይቶች ውስጥ ጠልቆ ለመግባት እና አካል ለመሆን በማሰቡ መሆኑን ግልጾ ነበር።
አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የድርጅቱ ሰራተኛ እንደገለጹት ለተቀነሱት ሰራተኞች ምንም አይነት የካሳ ክፍያ አልቀረበም። ይልቁንም ደመወዛቸው ውላቸው እስከሚያልቅ ድረስ ይከፈላቸዋል። ይህም እስከሚቀጥለው ወር ድረስ እንደሆነም ተናግረዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊት ኤሎን መስክ ለሚቀነሱ ሰራተኞች የ ሶስት ወር ደመወዛቸው በካሳ መልኩ እንደሚከፈላቸው የገለጸ ቢሆንም ስለየትኛው የትዊተር ቢሮ ለመግለጽ እንደፈለገ ግልጽ አላደረገም።
‘’ይህ ለእኛ አሳፋሪ ነው’’ ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት ሰራተኛ ተናግረዋል። በጋና የአገር ውስጥ ሕግ መሰረት ሰራተኞች በሚቀነሱበት ወቅት የካሳ ክፍያ መክፈል ብሎም የሶስት ወር ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መስጠት ግዴታ ነው። ትዊተር ግን ለሰራተኞቹ ከአንድ ወር ያነሰ የማስጠንቀቂያ ግዜ መስጠቱን ሰራኞቹ ተናግረዋል።
‘’ከኢሜይሉ በተጨማሪ ቀጣይ ሂደቶች ምን እንደሆኑ ያለማሳወቃቸው፤ ብቻ ሁሉም ነገር አሳፋሪ ነው’’ ሲሉ የድርጅቱ ሰራተኛ ተናግረዋል።
የጋና ቢሮ ሰራተኞች ይህ ኢሜይል ወደ ግል አካውንታቸው የተላከ ሲሆን የስራ ኢሜይላቸው ውስጥ መግባት እንዳይችሉ ተደርጓል።
ድርጅቱ በጋና የነበረው ቢሮ ከ 20 ያነሱ ሰዎችን የያዘ ነበር ሲሉ ምንጩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከትዊተር አስተዳዳሪዎች የተላከው ይሄው መልክት ሰራተኞች ከየትኛውም ደንበኛ፣ ባላስልጣናት፣ ባንኮች፣ አቅራቢዎች ብሎም ከሌሎች የድርጅቱ ሰራተኞች ጋር ምንም አይነት ንግግር እንዲሁም ግንኙነት እንዳይኖራቸው እና እነሱን ሊያናግሯቸው ከሞከሩም ለተቋሙ እንዲያሳውቁ ያስጠነቅቃል።
እንዲሁም የስራ ውላቸው እስከሚቋረጥ ድረስ ለሌላ ድርጅት እንዳይቀጠሩ ብሎም ግንኙነት እንዳይኖራቸው ኢሜይሉ ገልጿል። በዚሁ ኢሜይል ድርጀቱ መልካም ምኞቱን ገልጾላቸዋል።
የትዊተር አዲሱ ባለቤት መስክ ሰራተኞችን ከመቀነስ ውጪ ሌላ አማራጭ የለኝም ሲሉ ተናግረዋል። ለዚህም እንደምክንያት ያቀረቡት ድርጅታቸው በቀን ከ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ እያጣ መሆኑ ነው።
ትዊተር በጋና ያለውን ቢሮውን ሲከፍት በአገሪቱ ያለውን ሃሳብን በነጸነት የመግለጽ መብት እና የበይነ መረብ ነጻነት አሞግሶ ነበር። የጋና ፕሬዘዳንትም የዚህን ቢሮ መከፈት በማድነቅ እርምጃውን አሞግሰው ነበር።