ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የተዘጋጀው ብሔራዊ ቀብር ‘ውድ ነው’ ያለው ጃፓናዊ ራሱን አቃጠለ

የፎቶው ባለመብት, KYODO
ለቀድሞው የጃፓን ፕሬዝዳንት የተዘጋጀውን ብሔራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት በመቃወም አንድ ጃፓናዊ ራሱን በእሳት አቃጠለ።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በሰው እጅ ለተገደሉት ሺንዞ አቤ ቀብር በመቶዎች የሚቆጠሩ የውጭ አገራት መሪዎች ተጠርተዋል።
የጃፓን መንግሥት ያዘጋጀችው ይህ ብሔራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት በሚቀጥለው ሳምንት መስከረም 17/2015 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህንን ሥነ ሥርዓት በመቃወም ትላንት ማክሰኞ አንድ ጃፓናዊ ራሱን በእሳት ማቃጠሉ ተዘግቧል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ አቅራቢያ ግለሰቡ ራሱን ሲያቃጥል የተመለከቱ የዐይን እማኞች ለፖሊስ ደውለው አሳውቀዋል ።
ፖሊሶቹ በቦታው ደርሰው እሳቱን ካጠፉ በኋላ ግለሰቡን ወደ ሆስፒታል ወስደዋል።
ግለሰቡ ወደ ሆስፒታል ሲወሰድ ነፍሱን ያውቅ ነበር ተብሏል።
ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰበትና አሁን በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ገና አልታወቀም።
ግለሰቡ በ70ዎቹ ዕድሜ ክልል እንደሚገኝ የጃፓን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
መንግሥት ስለ ግለሰቡ ተቃውሞ እስካሁን አስተያየቱን አልሰጠም።
ሆኖም የሺንዞ አቤን ብሔራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚቃወሙ ጃፓናውያን ቁጥር ባለፉት ወራት እየጨመረ መጥቷል።
አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች ለቀብሩ ከፍተኛ ወጪ እየወጣ ነው ብለው ያምናሉ።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለፓርቲያቸው ቅስቀሳ ሲያደርጉ በአንድ ግለሰብ በተተኮሰባቸው ጥይት በ67 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል።
ግለሰቡ ራሱን ከማቃጠሉ አስቀድሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ አካባቢ ቀብሩን ሲቃወም እንደነበረ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ይገኛሉ። ፖሊስ ግን ገና አላረጋገጠም።
ግለሰቡ ራሱን ያቃጠለበት አካባቢ ቀብሩን የሚቃወም መልዕክት ያዘሉ ወረቀቶች እደተገኙም ተዘግቧል።
ጃፓንን ለረዥም ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ሺንዞ አቤ ግድያ ጃፓንን ሲያስደነግጥ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አውግዞታል።
ጃፓን ውስጥ እንዲህ ያለ በአደባባይ ላይ የሚከሰት ፖለቲካዊ ቀውስ ወይም የተኩስ ጥቃት የተለመደ አይደለም።
በበተጨማሪም በአገሪቱ ውስጥ ብሔራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓትም አልተለመደም።
የሺንዞ አቤን ብሔራዊ ቀብር እየተቃወሙ የሚገኙ ጃፓናውያን፣ ወደ 11.4 ሚሊዮን ዶላር የሕዝብ ገንዘብ የሚጠይቀውን ሥነ ሥርዓት ኮንነዋል።
ኮንስቲትዩሽናል ዴሞክራቲክ ፓርቲ የተባለው ተቃዋሚ ፓርቲ በቀጣዩ ሳምንት በሚካሄደው ብሔራዊ ቀብር እንደማይሳተፍ አስታውቋል።
ሺንዞ አቤን ተኩሶ የገደላቸው ግለሰብ እንዳለው፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዩኒፊኬሽን ከሚባል እምነት ጋር ትስስር ስላላቸው ነው የገደላቸው።
ይህ እምነት የቤተሰቦቹን ሃብት አሟጦ እንደወሰደም ተናግሯል።
የጃፓን የሕዝብ ተወካዮች ከዚህ እምነት ጋር ትስስር አላቸው በሚል ሌሎችም ጃፓናውያን ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።












