በባንግላዴሽ ባጋጠመ ፍንዳታ 50 ሰዎች ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቆሰሉ

እሑድ ድረስ እሳቱ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር አልዋለም ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እሑድ ድረስ እሳቱ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር አልዋለም ነበር
ታትሟል

በባንግላዴሽ ቺታጎንግ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ መጋዘን ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ እና ከፍተኛ ፍንዳታ በትንሹ 49 ሰዎች ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ቆስለዋል።

በሲታኩንዳ በሚባለው ስፍራ በርካታ የመርከብ ኮንቴይነሮች የፈነዱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እሳቱን ለማጥፋት ቦታው ከደረሱ በኋላ ነበር።

በአንዳንድ ኮንቴይነሮች ውስጥ ኬሚካሎች ሳይከማቹ አልቀረም ተብሎ ይገመታል።

የእሳት አደጋ በተደጋጋሚ የሚጎበኛት ባንግላዴሽ አሁን ያጋጠመው አደጋ ከዝቅተኛ የደህንነት አጠባበቅ ጋር ተያይዟል።

ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል በርካቶች በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን የሟቾች ቁጥርም ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል ተብሏል።

የአካባቢው ሆስፒታሎች ተጨናንቀዋል። ብዙ ሰዎች ህክምና ለማግኘት በየኮሪደሩ እየተጠባበቁ ይገኛሉ ተብሏል። የህክምና ባለሙያዎች ደም እንዲለገስ ጥሪ አቅርበዋል። አንዳንድ ተጎጂዎች በሄሊኮፕተር ወደ ርዕሰ ከተማዋ ዳካ ተወስደዋል።

እሳቱ ቅዳሜ  ምሽት የተቀሰቀሰ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ የእሳት አደጋ ሠራተኞች፣ ፖሊሶች እና በጎ ፈቃደኞች በፍጥነት በቦታው ደርሰዋል።

"ፍንዳታው ከቆምኩበት 10 ሜትር ያህል ገፍትሮ ወረወረኝ። እጆቼና እግሮቼ ተቃጥለዋል" ሲል የጭነት መኪና  አሽከርካሪው ቶፋኤል አህመድ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግሯል።

ነጠላ ጫማ ብቻ ያደረጉ በጎ ፈቃደኞችን ጨምሮ እሑድ ጠዋት ብዙዎች ከቃጠሎው ፍርስራሽ አስከሬን ለማውጣት ርብርባቸውን ቀጥለዋል።

ከአደጋው በኋላ የተጨማደዱ ኮንቴነሮች እና ጣሪያው የወደቀ መጋዘን ፎቶዎች በስፋት ተሰራጭተዋል። አንድ የሃገሬው ጋዜጠኛ ለቢቢሲ እንደገለጸው በአካባቢው መጥፎ ጠረን አለ።

እሑድ ድረስ ተጎጂዎችን የማውጣት ሥራ ሲከናወን ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እሑድ ድረስ ተጎጂዎችን የማውጣት ሥራ ሲከናወን ነበር

በፍንዳታው በትንሹ አምስት የእሳት አደጋ ተከላካዮች ህይወታቸውን አጥተዋል።  በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል። ከፍንዳታው በፊት ስለ ቃጠሎው ሲዘግቡ የነበሩ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ብዙዎች የደረሱበት አልታወቀም። 

ከፍተኛ የነበረው ፍንዳታ ከበርካታ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ይስማ ነበር ተብሏል፤። በአቅራቢያው ያሉትን ሕንፃዎች መስኮቶችም ሰባብሯል።

አንድ በአካባቢው የሚሠራ የሱቅ ባለቤት ለጋዜጠኞች እንደተናገረው ፍርስራሹ ግማሽ ኪሎ ሜትር በመምጣት በቀዬው አርፏል። ከፍንዳታው በኋላ “የእሳት እንደ ዝናብ ሲወርድ” ማየቱን ገልጿል።

በባንግላዴሽ የሚኖሩብዙ ሰዎች ፍንዳታውን እአአ በ2020 በቤሩት ከደረሰው ግዙፍ ፍንዳታ ጋር እያነጻጸሩት ነው።

ከቺታጎንግ የባንግላዴሽ ዋና የባህር ወደብ ስትሆን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማም ናት። በከተማዋ በሚገኘው ሲታኩንዳ አካባቢ ወደ 4,000 የሚጠጉ ኮንቴይነሮች በመጋዘኑ ተከማችተው ነበር።

መጋዘኑ እስከ 4000 ኮንቴነሮች ይይዛል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, መጋዘኑ እስከ 4000 ኮንቴነሮች ይይዛል