ባንግላዴሽ የሮሂንጃ ስደተኞችን ራቅ ወዳለች ደሴት በግድ እያጋዘች ነው ተባለ

የሮሂንጃ ስደተኞች ወደ ደሴቲቷ ሲወሰዱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የባንግላዴሸ ባለስልጣናት በሺዎች የሚቆጠሩ የሮሂንጃ ስደተኞችን ራቅ ወዳለች ደሴት በግድ እያጋዙ እንደሆነ ተገለጸ።

1 ሺህ 600 የሚቆጠሩ ስደተኞችም በተደጋጋሚ ጎርፍ ወደሚያጠቃት ባህሳን ቻር ወደተባለች ደሴትም እንደተወሰዱ ሮይተርስ ዘግቧል።

ባለስልጣናቱ ሁሉም በፈቃዳቸው ነው የተወሰዱት ቢሉም ስደተኞቹ በበኩላቸው ወደ ደሴቷ መሄድ እንደማይፈልጉ ለቢቢሲ ባለፈው ወር ተናግረው ነበር።

የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም እንዲሁ አርብ እለት የተወሰዱት ስደተኞች ያለ ፍቃዳቸው ነው በማለት ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል።

ሂውማን ራይትስ ዋች ፈቃደኛ ናቸው ተብለው ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት መካከል አስራ ሁለት ቤተሰቦችን ቃለ መጠይቅ ባደረገበት ወቅት ለመሄድ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አሳውቀውኛል ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታትም እንዲሁ ስደተኞቹን ስለማጓጓዝ የተሰጠው መረጃ ከቁጥር ውስጥ የማይገባ እንደሆነና በሂደቱም ባለስልጣናቱ አላሳተፉኝም በማለት አሳውቋል።

የባንግላዴሽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱል ሞመን በትናንትናው ዕለትም መንግሥታቸው "ማንኛውንም ስደተኛ በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ባህሳን ቻር አልወሰድንም። በዚሁ አቋማችንም እንፀናለን" ብለዋል።

የሮሂንጃ ስደተኞች ከሶስት ዓመት በፊት በሚያንማር የደረሰውን ወታደራዊ ጥቃትም በመሸሽ ነው የተሰደዱት።

በጥቃቱ 10 ሺህ ሰዎች እንደተገደሉና 730 ሺዎችም እንደተፈናቀሉ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በባንግላዴሽ ኮክስ ባዛር የስደተኞች ካምፕ በተጨናነቀ ሁኔታ እየኖሩ ነው።

የሮሂንጃ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሃምሳ አምስት ዓመቷ ራሺዳ ካቱን ባንግላዴሽ ያለፈቃዳቸው ወደ ባህሻን ቻር ካጋዘቻቸው 300 ስደተኞች መካከል ልጆቿ እንደሚገኙበት ለቢቢሲ ባለፈው ወር ተናግራ ነበር።

ልጆቿ ለተወሰኑ ወራትም ያህል የተሻለ ህይወት ፍለጋ በሚል ባንግላዴሽን ለቀው ለመውጣት በባሕር ላይ ሙከራ ሲያደርጉ ነበር።

የቢቢሲ ጋዜጠኞች ደሴቷን ለመጎብኘትና ስደተኞቹን ለማናገር እንዲሁ ባለፈው ወር ጠይቀው የነበረ ቢሆንም ውድቅ ተደርጎባቸዋል።

በዚሁ ሳምንት ሐሙስ የ31 ዓመት ግለሰብ ከኮክስ ባዛር ስደተኞች ካምፕ በአውቶብስ እየተጫነ እያለ ለሮይተርስ ደውሎ እያለቀሰ የሆነውን ተናግሯል።

"በግድ እያጋዙን ነው ያሉት። ከሦስት ቀናት በፊት ቤተሰቤ በዝርዝሩ ውስጥ እንዳለ ስረዳ ለመጥፋት ሞክሬ ነበረኝ። ትናንትና ግን ያዙኝና ያለ ፈቃዴ እየወሰዱኝ ነው" ብሏል።

የባንግላዴሽ ባለስልጣናት ባለፉት ሦስት ዓመታት በደሴቲቷ ላይ 350 ሚሊዮን ዶላር በሚያወጣ ወጪ ግንባታ እያካሄዱ ነበር።

የመንግሥትም ዋና አላማ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን መውሰድና በስደተኞቹ ካምፕ ውስጥ ያለውን መጨናነቅም እፎይታ መፍጠር ነው።

ሆኖም የሰብዓዊ ተሟጋቹ አምነስቲ ሪፖርት እንደሚያሳየው በደሴቲቷ 306 ስደተኞች እየኖሩ መሆኑን ገልፆ የአኗኗሯቸውንም ሁኔታ አሳዛኝ ነው ብሎታል።

በተጨናነቀና ንፅህናው ባልተጠበቀ ሁኔታ እንደሚኖሩና የምግብ እጥረት፣ የህክምና አቅርቦት በሌለበት ሁኔታና ቤተሰቦቻቸውንም ለማግኘት የስልክ አገልግሎት የላቸውም ብሏል-ሪፖርቱ።

ከዚህም በተጨማሪ በባሕር ኃይሉና የአካባቢው ወዛደሮች ወሲባዊ ትንኮሳና እንዲሁም ገንዘብ ካልሰጣችሁን የሚል ማስፈራሪያዎች እየደረሳቸው ነው ብሏል።

የባሕር ኃይሉ ቃለ አቀባይ ኮሞዶር አብዱላህ ማሙም ቻው ድሁሪ በበኩላቸው ክሱን ሐሰት ነው በማለት አጣጥለውታል "እንደ እንግዳ ነው እየተንከባከብናቸው ያለነው። ተመጣጣኝ ምግብ እየሰጠናቸው ነው። ማንኛውም አይነት አቅርቦት አላቸው" ብለዋል።