ስድስት ግብ የተቆጠረበት የአርሰናል እና ሼፊልድ ዩናይትድ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች አዲስ ታሪክ የጻፈ ሆኖ ተጠናቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትናንት ምሽት በተደረገ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ጨዋታ አርሰናል ከሜዳው ውጭ ከሼፊልድ ዩናይትድ ጋር ተጋጥሟል።
በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ሁሉንም ጨዋታዎች ያሸነፉት መድፈኞቹ፣ ግማሽ ደርዘን ግብ አስቆጥረው ተመልሰዋል።
የአርሰናል ፍጹም የበላይነት የነበረው ጨዋታ በርካታ አስገራሚ አስተያየቶች ተሰንዝረውበታል። በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አርሰናል በሼፊልድ ላይ ያሳረፈውን ብርቱ ጫና ተከትሎ የቢቢሲ ስፖርት ዘጋቢዋ ኤማ ስሚዝ “ጨዋታው የቦክስ ጨዋታ ቢሆን ኖሮ ዳኛው ያስቆመው ነበር” ብላለች።
በሼፊልድ ዩናይትድ እና አርሰናል መካከል የተደረገው ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የአንድ ቡድን ፍጹም የበላይነት የታየበት ነበር። አርሰናል አምስት ግቦችን ለማስቆጠር የወሰደበት ጊዜ 39 ደቂቃዎች ብቻ ነው።
80 በመቶ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው መድፈኞቹ፣ ካደረጓቸው ኢላማቸውን የጠበቁ ሰባት ሙከራዎች መካከል ወደ ግብነት ያልተቀየረችው አንዷ ብቻ ነች። ስድስቱን በተቃራኒ መረብ ላይ ማሳረፍ ችለዋል።
የስካይ ስፖርት ተንታኙ እና የቀድሞው የሊቨርፑል ተጫዋች ጂሚ ካራገር “ምናልባትም እስከዛሬ ካየኋቸው ደካማ የግማሽ ክፍለ ጊዜ ጨዋታዎች ይህኛው እጅግ የወረደው ሳይሆን አይቀርም” ብሏል።
“አርሰናል በኤፍኤ ካፕ ጨዋታ ከሁለተኛው ሊግ ወይም ከዚያ በታች ከሚገኙ ቡድኖች ጋር እየተጫወተ ቢሆን ኖሮ በመጀመሪያው አጋማሽ አምስት ለምንም ሊመራ አይችልም። በመሆኑም ይህ ውጤት በፕሪሚየር ሊጉ ለመቀበል የሚያዳግት ውጤት ነው” ብሏል ካራገር።
የሼፊልድ ዩናይትድ አሰልጣኝ ክሪስ ዋይልደር ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ “በጣም አሳዛኝ የውድድር ዘመን ነው። ብዙ የተጎዱ ተጫዋቾች አሉን። ሊጉ ሊያደርግ የሚችለው ይህንን ነው” ብለዋል።
ሊቨርፑልን ባስተናገድንበት ጨዋታ ያሳየነውን ብቃት ለመድገም ተመሳሳይ አሰላለፍ ይዘን ተጫውተናል፤ ነገር ግን የማይጠበቁ ቀላል የመከላከል ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውናል ብለዋል አሰልጣኝ ክሪስ ዋይልደር።
የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ደግሞ “ታላቅ ምሽት ነበር” ብሏል። “ጨዋታውን የጀመርንበት መንገድ ትልቅ ልዩነት ፈጥሯል፤ በበላይነት ተጫውተን ጥሩ ብቃት አሳይተናል” ብሏል የመድፈኞቹ አለቃ።
አርሰናል በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ ቢቆጣጠርም በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሚና ያለውን የግብ ብልጫ ለማግኘት አሁንም ግብ ለማስቆጠር በከፍተኛ ቁርጠኝነት ሲጫወት ነበር።
መድፈኞቹ በአሁኑ ወቅት 45 ንጹህ ግብ በመያዝ ከመሪው ሊቨርፑል በስድስት፣ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ማንችስተር ሲቲ ደግሞ በ10 የግብ ክፍያ ከፍ ብለው ተቀምጠዋል።
ሼፊልድ ዩናይትድ በሜዳው ያደረጋቸውን ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች አምስት እና ከዚያ በላይ ግቦችን በማስተናገድ የተሸነፈ የመጀመሪያው የፕሪሚየር ሊግ ቡድን ነው። በድምሩ በውድድር ዓመቱ ሼፊልዶች በሜዳቸው አራት ጊዜ አምስት እና ከዚያ በላይ ግቦችን አስተናግደው ተሸንፈዋል።
በአንጻሩ አርሰናል ያለፉትን ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳይቆጠርበት 17 ግቦችን በተቃራኒ የግብ መረብ ላይ በማሳረፍ ከፍተኛ ድል እየተጎናጸፈ ይገኛል።
አርሰናል በሳምንቱ መጨረሻ በሜዳው ብሬንትፎርድን ያስተናግዳል። መሪው ሊቨርፑል ደግሞ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ማንችስተር ሲቲን በአንፊልድ ያስተናግዳል። የእነዚህ ጨዋታዎች ውጤት ምናልባትም በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።












