የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ንግግር አነጋጋሪ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Facebook
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ማክሰኞ መጋቢት 05/2015 ዓ.ም. ለከተማው ምክር ቤት አባላት ያቀረቡት የአስተዳደራቸውን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ውስጥ የከተማዋን ፀጥታ በተመለከተ የተናገሩት አነጋጋሪ ሆኗል።
ከንቲባ አዳነች የአስተዳደራቸውን ያለፉት ስድስት ወራት የሥራ የአፈጻጸም ሪፖርትን ባቀረቡበት ወቅት የከተማዋን ፀጥታ እና ደኅንነት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ጊዜ “ሥልጣን በኃይል ለመቆጣጠር . . . ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ ፍልሰት እየተደረገ” ነው ብለው ነበር።
በዚህም ከንቲባዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት በመጣል ሥልጣንን በኃይል ለመቆጣጠር ከተማዋን ወደ አለመረጋጋት የማስገባት ተግዳሮቶች ገጥመውናል ብለዋል።
“በተለይም ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት የጽንፈኝነት፣ የጥላቻ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚደረጉ . . . ብዙ እንደቅስቃሴዎች ሲደረጉ እናስተውላለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ከንቲባ አዳነች ይህን ማለታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መነጋገሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የከንቲባዋ ንግግር “በማናቸውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው የዓለም አቀፍ ወንጀል ጥሪ ነው” ብሏል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከአብን በተጨማሪ እናት፣ መኢአድ እና ኢህአፓ የተባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሪፖርቱ ላይ ከተለያዩ ክልሎች ወደ ከተማዋ የሚገቡ ሰዎችን በተመለከተ የቀረበውን ሐሳብ አጥብቀው ተቃውመዋል።
ይህ ሁኔታም የዜጎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት የሚጻረር እና አሉታዊ ውጤትን የሚያስከትል ነው በማለት ከንቲባዋ በአዲስ አበባ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ያቀረቡትን ሪፖርት ነቅፈዋል።
አብን የዜጎች በነፃነት ተዘዋውሮ የመሥራት እና የመኖር መብት በአገሪቱ ሕገ-መንግሥትም ሆነ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተደነገጉ ናቸው በማለት መጋቢት 05/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ የከንቲባዋን ንግግር ተቃውሟል።
ፓርቲው “እንዲህ ዓይነት አደገኛ ቅስቀሳ በሪፖርትነት መሰማቱ እስካሁን ሲፈፀሙ ለነበሩ በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች እና እየታወጀ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ከለላ የሚሆን አደገኛ የወንጀል ድርጊት ጥሪ ነው" ብሏል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ረቡዕ ዕለት ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በቤት ልማት፣ በጤና፣ በውሃ አቅርቦት፥ በትምህርት፣ በትራንስፖርት ዘርፍ እና በገቢ አሰባሰብ የተከናወኑ ሥራዎችን ዘርዝረዋል።
119 ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መደራጋቸውን እና የኑሮ ጫና ለማቅለል ተከናውነዋል ያሏቸውን ሥራዎችን ዘርዝረዋል።
አማራ፣ ደቡብ እና ኦሮሚያ
ማክሰኞ በነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ የከተማዋን ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ናቸው የተባሉት ኃይሎች መነሻቸው አማራ፣ ደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች ናቸው ተብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ የሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ “ሰፊ የሆነ የፀረ ሰላም ኃይል በአዲስ አበባ ከተማ ማዕከል አድርጎ እየሰራ መሆኑ መታወቅ አለበት” ሲሉ ለከተማዋ ምክር ቤት አባላት የተናገሩ ሲሆን፣ በከተማዋ ያሉ የፀጥታ ስጋቶች በአራት ሚመደቡ ናቸው ብለዋል።
እንደ የከተማዋ የሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዋ ገለጻ ከሆነ ለመዲናዋ ስጋት የሆነው ቡድን ፖለቲካን፣ ብሔርን እና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ የፀጥታ ስጋት የሚፈጥር ሲሆን “ሌላኛው መደበኛ የወንጀል መከላከል ሥራዎችን ላይ ማዕከል አድረገው የሚነሱ የፀጥታ መድፈረሶች ናቸው” ብለዋል።
ሊዲያ ግርማ በዋናነት ከተማዋን እየፈተነ ያለው ሃይማኖታዊ እና ብሔርን መሠረት ያደጉ የአደባባይ በዓላትን መነሻ በማድረግ፣ የፖለቲካ ፍላጎት ያለው የተደራጀ ቡድን ኃይል ከክልል ወደ ከተማዋ እየገባ የሚፈጠረው ነው ብዋል።
“ከሁሉም ክልሎች ወደ ከተማ የሚገቡ ኃይሎች አሉ። ነገር ግን በተለይ በዓላት በሚመጡበት ጊዜ ከሦስት ክልሎች ከፍ ያለ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሰላም ለማደፍረስ ወደ ከተማዋ ይገባሉ። የመጀመሪያ ስፍራውን የሚይዘው ከአማራ ክልል የሚገቡት ናቸው” ብለዋል።
ከአማራ ክልል በመቀጠል “ሁለተኛው ከደቡብ ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ አዲስ አበባ ዙሪያ ካሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች ነው።”
ከሳምንታት በፊት ከአማራ ክልል ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ አዲስ አበባ ለመግባት የሞከሩ ሰዎች መከልከላቸውን እና ለቀናት መጉላላታቸውን እንዲሁም በርካቶች ወደየመጡባቸው አካባቢዎች መመለሳቸውን በመግለጽ አቤቱታ ሲያሰሙ እንደነበር ይታወሳል።
በተጨማሪም መሃል አዲስ አበባ ፒያሳ በሚገኘው የአጼ ምኒልክ አደባባይ የዓድዋ ድል በዓልን ለማክበር በወጡ ነዋሪዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ እና ድብደባ በመፈጸም ከልክ በላይ ኃይል መጠቀማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጾ ነበር።
ፖሊስ ባወጣው መግለጫ ላይ በበዓሉ ላይ ተፈጠረ ካለው ሁከት ጋር ተያይዞ 878 ተጠርጣሪዎች በቁጥር ስር መዋላቸው ተገልጾ “ከእነዚህም መከካከል 557 የሚሆኑት ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ናቸው” ብሎ ነበር።
ከዚህ የዓድዋ በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት የአንድ ሰው ሕይወት መጥፋቱን ፖሊስ ሲያስታወቅ፣ በርካቶች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሕክምና መወሰዳቸውን ተገልጿል።












