በኒው ዮርክ ሊጋጩ ስለነበሩት ሁለት አውሮፕላኖች ምርመራ ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ፣ ኒው ዮርክ ሁለት አውሮፕላኖች ሊጋጩ ተቃርበው የነበረ ሲሆን፣ ክስተቱን የአሜሪካ አቪየሽን ባለሥልጣን እየመረመረው ይገኛል።
አውሮፕላኖቹ ሙሉ በሙሉ ተሳፋሪዎች የጫኑ ሲሆኑ፣ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ነው ሊጋጩ የነበረው።
አንደኛው አውሮፕላን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሊበር የነበረ ቦይንግ 777፣ ሁለተኛው አውሮፕላን ደግሞ ወደ ዶምኒካን ሪፐብሊክ ሊበር የነበረ ቦይንግ 737 ነው።
አንደኛው አውሮፕላን እያኮበኮበ የነበረ ሲሆን፣ እያኮበኮበ በነበረበት መንገድ ላይ ሌላኛው አውሮፕላን እየተንቀሳቀሰ ነበር።
ሁለቱን አውሮፕላኖች ሊጋጩ እንደሆነ ያስተዋለ የበረራ ተቆጣጣሪ ጣልቃ ገብቶ አደጋ ሳይከሰት ቀርቷል።
ከበረራ ጋር የተያያዙ የመልዕክት ልውውጦችን የሚከታተለው ላይቭኤቲሲ ድረ ገጽ ይፋ ባረገው የድምጽ ቅጂ መሠረት የበረራ ተቆጣጣሪው “ዴልታ 1943 ለበበራ ዝግጁ ምልክት ተቀልብሷል ” በማለት ነው አደጋው እንዳይከሰት ያስቻለው።
ይህን ማስጠንቀቂያ የሰማው የዴልታ አየር መንገድ ቦይንግ 737 መንደርደሪያው ላይ ቆሟል። የአሜሪካን አየር መንገድ ቦይንግ 777 ደግሞ በሌላኛው አውሮፕላን ፊትለፊት በሰላም እንዳለፈ የአሜሪካ አቪዬሽን ባለሥልጣን ገልጿል።
አውሮፕላኖቹ አንዳቸው ከሌላቸው በ1,000 ጫማ ልዩነት እንደነበሩም አክሏል።
የዴልታ አየር መንገድ አውሮፕላን 145 ተሳፋሪዎች እና ስድስት የበረራ ሠራተኞች ነበሩት። የአሜሪካን አየር መንገድ ደግሞ 137 ተሳፋሪዎች እና 14 የበረራ ሠራተኞች ጭኖ ነበር።
የዴልታን አውሮፕላን ተሳፍረው ከነበሩት አንዱ የሆነው ብራየን ሄል ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደተናገረው፣ አውሮፕላኑ ድንገት ሲቆም የቴክኒክ ችግር የገጠመው መስሎት ነበር።
“ድንገት አውሮፕላኑ ሲቆም ሁላችንም ከወገባችን ወደፊት ሸርተት አልን” ብሏል ተሳፋሪው።
ዴልታ አየር መንገድ ለምርመራው እንደሚተባበር ገልጿል። አሜሪካን አየር መንገድ ግን እስካሁን ስለ ክስተቱ መግለጫ አላወጣም።












