ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባንክ ሊዘርፍ እንደነበረ የተጠረጠረ ግለሰብ በቱቦ ውስጥ ከገጠመው አደጋ ተረፈ
ፖሊስ ባንክ ለመዝረፍ እየተጓዝ ሊሆን ይችላል በሚል የጠረጠረው አንድ ጣሊያናዊ ግለለሰብ ቫቲካን አቅራቢያ በሚገኝ ቱቦ ውስጥ ከገጠመው አደጋ የነፍስ አድን ሠራተኞች ታድገውታል።
የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ጣሊያናዊውን ግለሰብ ሕይወት ለማትረፍ ከመኪና መንገድ በታች የሚገኝ የፍሳሽ ማስተላለፊያ ጋር ለመድረስ 8 ስዓታት የፈጀ ቁፋሮ ማድረጋቸውም ተሰምቷል።
ከጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ እንዲወጣ የተደረገው ግለሰብ በአሁኑ ጊዜ በሆስፒታል ውስጥ እየተደረገለት ባለው ክትትል እያገገመ ነው።
ፖሊስ ግለሰቡን እና ሌሎች ሁለት ሰዎችን የሕዝብ ንብረት በማውደም ወንጀል ሊከሳቸው እየተዘጋጀ ይገኛል። የፖሊስ መኮንኖች ሰውዬው ባንክ ሊስረስሩ የሚሞክሩ ወሮበሎች አባል ሳይሆን እንደማይቀር ጠርጥረዋል።
ከስፍራው ለማምለጥ የሞከሩት ሌሎቹ ሁለት ግለሰቦች ለፖሊስ መኮንኖች ሥራ ተባባሪ ባለመሆን ተከሰው መታሰራቸውን የጣሊያን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ባንክ ለመዝረፍ ሲሞክሩ እንደነበሩ ከጠረጠሩት ግለሰቦች ሦስቱ ዋሻው ከመናዱ በፊት ራሳቸውን ከአዳጋው አትርፈው ያመለጡ ሲሆን፣ አሁን ሆስፒታል የሚገኘው ግለሰብ ግን ስድስት ሜትር ጥልቀት ባለው ጉድጓድ ውስጥ ተቀርቅሮ ተገኝቷል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ለፈረንሳይ የዜና ወኪል “ምርመራችን እንደቀጠለ ነው። ግለሰቦቹ ዘራፊዎች ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ገና አልደረስንም” ብለዋል።
ባዶ እና አዲስ ከተከራዩ ሱቆች ስር የሚገኛው የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ለሁለት ባንኮች ቅርበት ያለው ነው።
ሆኖም የጣሊያን መገናኛ ብዙኃን ግለሰቦቹ ከተማው ጭር በሚልባቸው የእርፍት ቀናት ውስጥ ከባንክ አቅራቢያ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ ማገኘታቸው አላማቸው ምን እንደሆነ በግልጽ ያሳያል የሚሉ ዘገባዎችን እያወጡ ይገኛሉ።
በአካባቢው ላይ ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ እዚህ አከባቢ እየተደረገ ስላለው ነገር ምንም መረጃ የለንም ብሏል። “ሁላችንም አካባቢው ላይ የነበሩት ሰዎች እድሳት ላይ ናቸው ብለን ነበር ያስብነው” ብሏል።