በዩክሬን የተገደሉ የሩሲያ ወታደሮች ቁጥር 50 ሺህ መድረሱን ቢቢሲ አረጋገጠ

በዩክሬን የተገደሉት የሩሲያ ወታደሮች ቁጥር ከ50 ሺህ ማለፉን ቢቢሲ አረጋገጠ።
ሁለት ዓመት ባስቆጠረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ሞስኮ “የስጋ መፍጫ” የምትለውን ስለት እየተገበረች ባለችብት ሰዓት የሞቱ ወታደሮቿ ቁጥር ካባለፈው ዓመት በ25 በመቶ መጨመሩን ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት ማረጋገጥ ተችሏል።
የቢቢሲ የሩሲያ ቢሮ፣ ሚዲያዞና የተባለ ገለልተኛ ቡድን እንዲሁም በጎ ፍቃደኞች ከአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 ጀምሮ የሟቾችን ቁጥር ሲመዘግቡ ቆይተዋል።
በሩሲያ አዲስ የተመሰረተው የመቃብር ስፍራ ሟች ወታደሮችን በስም ለመለየት ረድቷል።
በተጨማሪም ቢቢሲ ለህዝብ ክፍት የሆኑ እንደ መንግሥታዊ ሪፖርቶች፣ ጋዜጦች እና የማህበራዊ ሚዲያ ምንጮችን ለመረጃነት ተጠቅሟል።
ታዲያ ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት ሁለተኛ ዓመቱን ባስቆጠረው ውጊያ ከ27 ሺህ 300 በላይ የሩሲያ ወታደሮች መገደላቸውን ተረድቷል። ይህም ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶች ለመያዝ ከፍተኛ የሰው ሕይወት መክፈሏን ያመለክታል።
ሩሲያ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፍቃደኛ ስትሆን ቀርታለች።
“የስጋ መፍጫ” የተሰኘው ቃል ሩሲያ የዩክሬንን ሠራዊት በከባድ መሳሪያ ለመምታት ያለማመንታት የምትለከውን የሰው ማዕበልን ለማመልከት የሚውል ነው።
ቢቢሲ የደረሰበት የሟች ወታደሮች ቁጥር ሞስኮ በአውሮፓውያኑ 2022 ይፋ ካደረገችው አሃዝ በ8 እጥፍ የሚልቅ ነው።
የሞቱት ወታደሮች ትክክለኛ ቁጥር ግን ከዚህም ከፍ ያለ እንደሆነ ይታመናል።
ሩሲያ በምስራቃዊ ዩክሬን ተቆጣጥራ በያዘቻቸው ዶኔስክ እና ሉሃንስግ የሞቱ የሩሲያ ሚሊሻዎች ቁጥር በዚህ ዘገባ ውስጥ አልተካተተም።
ይህ ቁጥር ቢጨምር በሩሲያ በኩል የሞቱት ወታደሮች ቁጥር አሁን ከተጠቀሰው ሊጨምር ይችላል።
በሌላ በኩል ዩክሬን ስለሞቱባት የወታደሮች ቁጥር እምብዛም አስተያየት ስትሰጥ አይሰማም።
ሆኖም ባለፈው የካቲት ወር ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ 31 ሺህ የዩክሬን ወታደሮች መገደላቸውን አመላክቷል።
ይሁን እንጂ የአሜሪካ ደኅንነት የሟቾች ቁጥር ከዚህ ከፍ ያለ እንደሆነ አመልከቷል።












