የለንደን ደርቢ፡ ሁለቱ አሰልጣኞች ለምን ቀይ ካርድ ተመዘዘባቸው?

ኮንቴ እና ቱሄል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ስታምፎርድ ብሪጅ ለአሰልጣኞች ፍጥጫ እና የደስታ መፈንጫ ቦታ መሆንን ቀጥሎበታል።

የቼልሲው አሰልጣኝ ቶማስ ቱሄል እና የቶተንሃሙ አቻቸው አንቶኒዮ ኮንቴ ቡጢ ቀረሽ ግብግብ ውስጥ በመግባታቸው ሁለቱም ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ ቀይ ካርድ ተመዞባቸዋል።

“አየሩም፣ ሜዳውም፣ ጨዋታውና ተቀያሪ ቦታውም ሁሉም ሞቅ ያለ ነበር፥ እንዲህ ዓይነት ጨዋታ በውድድሩ ጅማሬ ላይ መሆኑ ያስደስታል” ሲሉ ቱሄል ከጨዋታ በኋላ ፈገግ ብለው አስተያየት ሰጥተዋል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ፍትጊያ የበዛበት ጨዋታ እሰከ 68ኛው ደቂቃ ድረስ የተረጋጋ ይመስል ነበር።

ካሊዱ ኩሊባሊ ክለቡ ቼልሲን መሪ ማድረግ ችሎ ነበር። ፒዬር-ኤሚል ሆቢዬር ቶተንሃምን አቻ ያደረገች ጎል ማስቆጠሩ የጨዋታውን መልክ ቀየረች።

ከጎሉ ህጋዊነት ጋር ተያይዞ ሁለቱ አሰልጣኞች ተፋጠው በአራተኛው ዳኛ ገላጋይነት ተለያዩ።

ሁለቱም የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ ተመዘዘባቸው።

ጎሉ ከመቆጠሩ በፊት ካይ ሃቨርትዝ ጥፋት ተፈጽሞበታል የሚል ነው የቼልሲ ክስ። የቶተንሃሙ ሪቻርለሰን ጎሉ ሲቆጠር ከጨዋታ ክልል ውጭ ከመሆን ባለፈ የግብ ጠባቂውን እይታ ከልሎታል የሚልም ቅሬታ በቼልሲ ቀርቦ ነበር።

ከዘጠኝ ደቂቃ በኋላ ሪስ ጀምስ በድጋሚ ቼልሲን ቀዳሚ አደረገ። ቱሄል በደስታ እየቦረቁ ሲሮጡ ታዩ።

በተጨማሪ ስድስት ደቂቃዎች ሃሪ ኬን በጨዋታም በጎልም ተበልጦ የቆየውን ቡድኑን አቻ ለማድረግ በቃ።

የመሐል ዳኛው ጨዋታው መጠናቀቁን የሚያበስረውን ፊሽካ አሰሙ። እንደተለመደው አሰልጣኞቹ ተጨባብጠው ሊለያዩ ነው ሲባል ተጨባብጠው የእጃቸውን ጥንካሬ ይፈትሹ ገቡ።

ይህ ደግሞ ወደ ግብግብ አምርቶ ሁለቱም ቀይ ካር ለማየት በቁ።

ኬን ከማስቆጠሩ በፊት ክርስቲያን ሮሜሮ የቼልሲውን አዲስ ፈራሚ ማርክ ኩኩሬላን ጸጉር ስቧል የሚል ሌላ ቅሬታ በቼልሲ ቀረቧል።

“ሁለቱም ጎሎች በቫር ዘመን መጽደቅ አልበረባቸውም። ዳኛው ትልቅ ሚና መጫወት ነበረባቸው” ሲሉ ቱሄል ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“የመጀመሪያው ጎል እንዴት ከጨዋታ ውጭ እንዳልሆነ እና ሁለተኛው ደግሞ ቀይ ካርድ አለመሆኑ አልገባኝም” ብለዋል።

የመሐል ዳኛው ቴይለር ወደፊት የቼልሲን ጨዋታ መምራት የለባቸውም ሲሉም ቅሬታ አሰምተዋል።

ሲጨባበጡም የመከባበር ነገር ከኮንቴ በኩል እንዳላዩ የቼልሲው አሰልጣኝ ገልጸዋል።

“ሰው ሲጨባበጥ ዓይን ለዓይን መተያየት ያለብን ይመስለኛል። ብቻ ብዙ ነገሮች ትክክል አልነበሩም” ብለዋል።

ኮንቴ ግን በጉዳዩ ላይ ብዙም ማውራት የፈለጉ አይመስሉም። “ችግር ካለ በእኔ እና በእሱ መካከል ነው” ብለዋል።

“በተፈጠረው ክስተት ተዝናንተናል። በሚቀጥለው ጊዜ ስንጨባበጥ ችግሩን እንፈታዋለን። እኔም በቦታዬ እሱም በቦታው እንቀመጣለን” ሲሉ አክለዋል።

ቱሄል ሁለተኛው ጎል ሲቆጠር እየዘለሉ ደስታቸውን በመግለጻቸው ግማሽ ይቅርታ ጠይቀዋል።

“መሐል ላይ ማድረግ እንደሌለብኝ ተሰምቶን ነበር። ግን አንዳንድ ጨዋታዎች እንደዚህ ያደርጋሉ” ብለዋል።

CHETOT

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፕሪሚየር ሊጉ ከተጀመረ በኋላ ቶተንሃም ስታምፎርድ ብሪጅ አይቀናውም። ወደ ሰማያዊዎቹ ሜዳ አቅንቶ 22 ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ብቻ ሲያሸንፍ 12 ጊዜ አቻ ተለያይቷል።

“ብዙ ጊዜ በስታፎርድ ብሪጅ አይቀናንም። ስለዚህ ባለቀ ሰዓት ጎል አስቆጥረን አንድ ነጥብ ማግኘታችን አስደስቶናል” ያለው የቶተንሃሙ አምበል ሃሪ ኬን ነው።

“ቀይ ካርዶቹን መመልከት ያሳዝናል። በስሜት የተሞላ የለንደን ደርቢ ነበር። ሁለቱም ቡድኖች ለማሸነፍ ተጫውተዋል። አንዳንዴ ተመሳሳይ ነገር ያጋጥማል” ብሏል።

ሌላ ውድድር ካላገናኛቸው በስተቀር የትናንቱ ጨዋታ በየካቲት የሚደረገው የሁለቱ ቡድኖች ግጥሚያ ከወዲሁ በጉጉት እንዲጠበቅ በር ከፍቷል።