የዩክሬን ጦርነት: ፑቲን እያጠፋችሁ ነው ሲሉ ዜለንስኪ ለሩሲያውያን ተናገሩ  

ዜሌንስኪ
ታትሟል

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ መሪያችሁ አገራችሁን እያፈራረሰ ነው ሲሉ ለሩሲያውያን መልዕክት አስተላለፉ።

ቭላድሚር ፑቲን የውትድርና ዩኒፎርም በለበሱ ሰዎች መሃል በመሆን የአዲስ ዓመት ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው ዜለንስኪ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ከወታደሮቻቸው ጀርባ እየተሸሸጉ እንጂ እየመሯቸው አይደለም ያሉት።

ቅዳሜ በመላው ዩክሬን ሕይወት ያጠፉ ጥቃቶች የቀጠሉ ሲሆን ዩክሬናውያን ሩሲያን ይቅር እንደማይሉ ዜለንስኪ ተናግረዋል።

በጥቃቶቹ ቢያንስ አንድ ሰው ሲሞት በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል።

የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ከገባ በኋላም እሁድ በኪዬቭ ላይ ተጨማሪ የሚሳኤል ጥቃቶች መሰንዘራቸውን ባለስልጣናት ተናግረዋል። በሰው ሕይወት ላይ ስለደረሰ ጉዳት እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም።

የዩክሬን ጦር ኃይሎች መሪ ቫለሪ ዛሉዥኒ የአየር መከላከያዎች ከ20 የሩስያ ሚሳኤሎች 12ቱን ማክሸፋቸውን ቅዳሜ ተናግረዋል።

ጥቃቶቹ የተከሰቱት ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከታዩት ከፍተኛ የአየር ድብደባዎች አንዱ ከተፈጸመ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የተሰነዘሩ ጥቃቶች ለተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ ምክንያት ሆነዋል።

ሞስኮ ሲቪሎችን ዒላማ ማድረጓን ደጋግማ ብትክድም ፑቲን በቅርቡ ወሳኝ የሆኑ የኃይል ተቋማትን መምታታቸውን አምነዋል።

ዜለንስኪ በቴሌግራም ቻናላቸው ባስተላለፉት መልዕክት የቅዳሜው ጥቃት ያደረሱትን ኢሰብዓዊ ናቸው ብሏል።

ቋንቋቸውን ከዩክሬንኛ ወደ ሩስኪ በመቀየር ፑቲንን አጥቅተዋል።

ፑቲን ከወታደሮቻቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"መሪያችሁ ከፊት እየመራ ወታደሮቹ ደግሞ ከኋላ መሆናቸውን ሊያሳያችሁ ይፈልጋል" ብለዋል።

“እውነታው ግን እሱ ተደብቋል። ከጦር ኃይሉ፣ ከሚሳኤሎቹ፣ ከመኖሪያ ቤቱ እና ከቤተ መንግስቶቹ ግድግዳ ጀርባ ተደብቋል።“

"ከኋላ ተደብቋል። አገራችሁን እና የወደፊት ሕይወታችሁን እያቃጠለ ነው። ማንም ለሽብር ይቅር አይልም። ማንም በዓለም ላይ ይቅር አይልም። ዩክሬንም ይቅር አትልም" ብለዋል።

በአዲስ ዓመት መልካም ምኞታቸው ዜለንስኪ የሩስያን ግስጋሴ ለመቀልበስ ላደረጉት "አስደናቂ" ጥረት ዩክሬናዊያንን አመስግነዋል። 

“ሁሉም ክልሎች እና መላ አገሪቱ እንደ አንድ በጋራ እንዋጋለን። ሁላችሁንም አደንቃለሁ። ሁሉንም የማይበገር የዩክሬን ክልል ማመስገን እፈልጋለሁ" ብለዋል።

ፑቲን ለፈረንጆቹ 2023 ለእያንዳንዱ የሩሲያ 11 የሰዓት ዞኖች የተሰራጨውን የአዲስ ዓመት መልዕክት አስተላለፍዋል።

የሩሲያው መሪ የአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አደጋ ላይ ነው በማለት በዩክሬን ውስጥ ከሚዋጉት ወታደሮቻቸው ጀርባ ዜጎቻቸውን ለማሰባሰብ ሞክረዋል።

ፑቲን እንዳሉት “ሁሌም እንደምናውቀው፤ ዛሬም እንደገና እንደተረጋገጠልን የሩሲያ ሉዓላዊ፣ ገለልተኛ እና አስተማማኝ ህልውና በእኛ ጥንካሬ እና ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው" ብለዋል። 

የዩክሬንን ወረራ “ህዝቦቻችንን እና ታሪካዊ መሬቶቻችንን እንጠብቃለን። ሞራላዊ፣ ታሪካዊ ትክክለኛነት ከጎናችን ነው” ብለዋል።

ሞስኮ የዩክሬን ላይ ወረራ እንድትጀምር “መነሾ ሆነዋል” በማለት ፑቲን ምዕራባውያንን ከሰዋል።

"ምዕራባውያን ስለሠላም ዋሽተው ነበር። ለጥቃት እየተዘጋጁ ነበር ... አሁን ደግሞ ዩክሬንን እና ሕዝቦቿን ሩሲያን ለማዳከም እና ለመለያየት እየተጠቀሙ ነው” ብለዋል።