የቀድሞው የቶተንሃም ተጫዋች በጭማሪ ሰዓት ያስቆጠራት ጎል የልጅነት ክለቡ ከ66 ዓመታት በኋላ ዋንጫ እንዲያነሳ አስቻለች

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport
የቀድሞው የቶተንሃም ተከላካይ ቶቤ አልደርቪረልድ በጭማሪ ሰዓት ባስቆጠራት ጎል የልጅነት ክለቡ ከዘመናት በኋላ ዋንጫ እንዲያነሳ አስቻለች።
የቤልጂየሙ ሮያል አንትዌርፕ እሑድ ዕለት ድራማ በተሞላበት ጨዋታ ከ66 ዓመታት በኋላ ዋንጫ አንስቷል።
ሬሲንግ ጌንክ፣ ዩኒየን ኤስጂ እና ሮያል አንትዌርፕ የተባሉት ሦስት ክለቦች ዋንጫ የማንሳት ዕድል ነበራቸው።
የአልደርቪረልድ ክለብ አንትዌርፕ ከጌንክ በነበራቸው ጨዋታ ባለሜዳው ጌንክ እስከ ጭማሪ ደቂቃ 2-1 ሲመራ ቆየ።
ነገር ግን በ94ኛው ደቂቃ ቶቢ አልደርቪረልድ ወደ ጎል አክርሮ የመታት ኳስ ከመረቡ አረፈች።
ዋንጫ ለማንሳት አቻ ውጤት በቂያቸው የነበረው ሮያል አንትዌርፕ ከ66 ዓመታት በኋላ የቤልጂየም ሊግ ቻምፒዮን ሆነዋል።
ባለፈው ዓመት ከካታሩ አል-ዱሃይል ወደ ልጅነት ክለቡ አንትዌርፕ የመጣው አልደርቪረልድ “እኔ ቃላት የሉኝም” ሲል ደስታውን ገልጧል።
“ማንም ለኛ ግምት አልሰጠንም። በጣም ታግለናል። ሁሉም ከኛ ተቃራኒ ነበር። ነገር ግን አደረግነው።”
አንትዌርፕ በአንድ ነጥብ ከጌንክ እና ዩኒየን በልጦ የቤልጂየም ሊግ ባለድል ሆኗል።
ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ለዋንጫ ከጫፍ ደርሶ በሜዳው በመሸነፉ ምክንያት ዋንጫ ሳያነሳ ቀርቷል።
በእሑዱ ፍልሚያ ከዋንጫ ተፎካካሪዎች መካከል አንዱ የነበረው ዩኒየን ኤስጂ ላለፉት 88 ዓመታት ሊጉን አሸንፎ አያውቅም።
አልደቪረልድ በጭማሪ ደቂቃ ጎል ሲያስቆጥር የጌንክ ደጋፊዎች በድንጋጤ ዝምታ ሰፍኖባቸዋል።
አሠልጣኝ ማርክ ቫን ቦሜል ወደሜዳ ዘልቀው ከተጫዋቾቻቸው ጋር ደስታቸው ሲገልጹ ተስተውለዋል።
የቀድሞው የቶተንሃምና የቤልጂየም ተከላካይ የነበረው የ34 ዓመቱ አልደርቪረልድ ግማሽ ሜዳ ሮጦ ከአንትዌርፕ ደጋፊዎች ጋር ደስታውን ተጋርቷል።
በሌላ በኩል የብራይተኑ ባለቤት ቶኒ ብሉም ንብረት የሆነው ዩኒየን በክለብ ብሩገ ተሸንፏል።












