ዝላታን ኢብራሂሞቪች፡ ስዊዲናዊው የእግር ኳስ ኮከብ በ41 ዓመቱ ጫማ ሰቀለ

ኢብራ

የፎቶው ባለመብት, MATTEO BAZZI/EPA-EFE/REX/Shutterstock

ታትሟል

የኤሲ ሚላኑ ዝላታን ኢብራሂሞቪች በ41 ዓመቱ ጫማ ሰቀለ።

በዘመናዊው እግር ኳስ አሉ ከሚባሉ ድንቅ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ኢብራ ኳስ በቃኝ ብሏል።

“እግር ኳስ እሰናበታለሁ። እናንተን ግን መሰናበት አልችልም” ሲል የሚላንን ሳን ሴሮ ሜዳ ለሞሉ ደጋፊዎቹ ተናግሯል።

ኢብራሂሞቪች አስቀድሞ ከጣሊያኑ ክለብ እንደሚለቅ እንጂ ጫማ እንደሚሰቅል አልነበረም ያስታወቀው።

511 የክለብ ጎሎች ያስቆጥው ኢብራ ለፒኤስጂ፣ ለማንቸስተር ዩናይትድ፣ ለኤሲ እና ኢንተር ሚላንና ለሌሎችም ክለቦች ተጫዋቷል።

በአራት የተለያዩ ሃገራት ዋንጫዎችን አንስቷል።

ኢብራሂሞቪች ለሁለተኛ ጊዜ ለኤሲ ሚላን የፈረመው በፈረንጆቹ 2020 ነበር። ከዚህ ቀደም በ2011 የጣሊያን ስኩዴቶን ከሚላን ጋር ማንሳት ችሏል። ባለፈው ዓመትም ይህን ደግሟል።

ነገር ግን በተገባደደው የውድድር ዘመን በጉዳት ምክንያት ብዙ አልተጫወተም።

“አሁን በጣም ስሜታዊ ሆኛለሁ። ፎርዛ ሚላን። ሁላችሁም ደኅና ሁኑ” ሲል ሳግ እየተናነቀው ተሰናብቷል።

“መጀመሪያ ስመጣ ደስታ ሰጣችሁኝ። ሁለተኛ ስመጣ ደግሞ ፍቅር። እጃችሁን ዘርግታችሁ ተቀበላችሁኝ። እንደቤት እንዲሰማኝ አደረጋችሁኝ። ለቀሪው ሕይወቴ እኔ የሚላን ነኝ።”

14 የሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ 34 ዋንጫ ያነሳው ኢብራ 11 ጊዜ ለባለን ደኦር ታጭቷል።

የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ አንስቶ የማያውቀው ኢብራ የአውሮፓ ሊግ ዋንጫን ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር በ2017 ማንሳቱ ይታወሳሉ።

122 ጊዜ ለስዊድን የተሰለፈው ኢብራሂሞቪች በ66 ጎሎች የብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ነው።

በወርቅ የተለበጠ የእግር ኳስ ዘመን

ኢብራሂሞቪች በፈረንጆቹ 1999 ፕሮፌሽናል እግር ኳስ የጀመረው ባደገበት ከተማ በሚገኘው ማልሞ ኤፍኤፍ ነው።

በ2001 ወደ አያክስ አቅንቶ በሶስት ዓመት ቆይታው ሶስት የሊግ ዋንጫዎችን አነሳ።

በ2004 ወደ ጣሊያን አቅንቶ ጁቬንቱስን ተቀላቀለ። በቆይታው ሁለት የሴሪአ ዋንጫ ቢያነሳም ሁለቱም ዋንጫዎች በጁቬንቱስ የካልቺዮፖሎ ቅሌት ምክንያት እንዲሰረዙ ሆነዋል።

ኢብራ ወደ ባርሴሎና ከማቅናቱ በፊት ወደ ኢንተር ሚላን ሄዶ ሶስት ጊዜ የጣሊያን ሴሪ አ ባለቤት ሆነ።

ኢብራሂሞቪች በካታላኑ ክለብ ለአንድ የውድድር ዘመን ብቻ ቢቆይም ላ ሊጋውን አንስቶ በውሰት ኤሲ ሚላንን ተቀላቀለ።

ቀጥሎ የፈረንሳዩን ፒኤስጂ የተቀላቀለው ኢብራ በ122 የሊግ ጨዋታዎች 113 ገሎችን ሲያስቆጥር አራት ጊዜ የሊግ 1 ዋንጫዎችን አንስቷል።

ሐምሌ 2016 ለማንቸስተር ዩናይትድ የፈረመው ስዊዲናዊው ኮከብ ከቀያይ ሰይጣኖቹ ጋር የአውሮፓ ሊግና የሊግ ዋንጫን አነሳ።

ኢብራ ወደ ኤሲ ሚላን ከመመለሱ በፊት ለአሜሪካው ኤል ኤ ጋላክሲ ፈርሞ ካሊፎርኒያ ሁለት ዓመት ቆይቶ ነው የመጣው።