ዩክሬን በክሬሚያ የሚገኝን የሩስያ ባህር ሰርጓጅ መርከብን መትታ ማስጠሟን አስታወቀች

ሮስቶቭ-ኦን-ዶን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዩክሬን ጦር የክራይሚያ ባሕረ ገብ ወደብ ላይ ቆሞ የነበረ የሩሲያ ባህር ሰርጓጅ መርከብ ላይ ጥቃት ከፍቶ ማውደሙን አስታወቀ።

እአአ በ2014 ሥራ የጀመረው ሮስቶቭ-ኦን-ዶን የተሰኘው ሰርጓጅ መርከብ አርብ ዕለት ከወደብ ከተማዋ ሴቫስቶፖል በተተኮሰ ሚሳኤል ከተመታ በኋላ መስጠሙን የዩክሬን ጦር በመግለጫ ላይ ይፋ አድርጓል።

ሰርጓጅ መርከቡ ረጅም ርቀት ተመዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፍ ከሚችሉ እና በሩሲያ ጥቁር ባህር ከሚንቀሳቀሱት አራት ሰርጓጅ መርከቦች አንዱ እንደነበር ተዘግቧል። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ምንም አስተያየት አልሰጠም።

የኪዮቭ ባለስልጣናት አክለውም በጥቃቱ በ2014 ሩሲያ በህገ-ወጥ መንገድ የወሰደችውን ባሕረ ገብ መሬት የሚጠብቁ አራት ኤስ-400 የአየር መከላከያዎች ወድመዋል ብሏል።

ባለፈው መስከረም ወር ሮስቶቭ ኦን-ዶን በሴባስቶፖል የመርከብ ጣቢያ ጥገና ላይ እያለ በሚሳኤል ጥቃት “አስከፊ ጉዳት ደርሶበት ሊሆን ይችላል” ሲሉ በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ የስለላ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የዩክሬን ጦር እንደገለፀው ሩሲያ መርከቡን እንደጠገነች እና ዋጋው 300 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነም አክለዋል።

ሩሲያ እአአ በ2024 ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ ዋና ዋና የሚባሉ የባህር ኃይል ውድመቶችን አስተናግዳለች። ዩክሬን የጥቁር ባህር መርከቦች ምልክት የሆነችውን ሞስኮቫን ጨምሮ ቢያንስ 15 የጦር መርከቦችን ክፉኛ ጎድታለች ወይም አስጥማለች።

ባለፈው ሳምንት ሞስኮ በመርከቦቿ ላይ የደረሰውን ተደጋጋሚ ጥቃት ተከትሎ ሁሉንም የባህር ኃይል ንብረቶቿን ከአዞቭ ባህር እንድታወጣ መገደዷን የዩክሬን ጦር ተናግሯል።

የሩስያ የአገር ውስጥ ደኅንነት አገልግሎት ኤፍኤስቢ በበኩሉ በቅርቡ የዩክሬን የቀረውን የአውሮፕላን ተሸካሚ አድሚራል ኩዝኔትሶቭን ለማጥቃት ያቀደችውን ሴራ ማክሸፉን ተናግሯል። እአአ በ1985 የተሠራችው መርከቧ ከ 2018 ጀምሮ ጥገና ላይ ትገኛለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች በሩሲያ ዋና ዋና የአየር ማረፊያ እና የነዳጅ ማከማቻ ቦታዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን የኪዬቭ ባለስልጣናት ገለጸዋል።

ጥቃቱ ያነጣጠረው በሞሮዞቭስክ አየር ማረፊያ ሲሆን በቅርብ ጊዜ በዩክሬን ከተሞች ላይ ከፍተኛ ውድመት ያደረሱ ፈንጂዎች የተከማቹበት ስፍራ ነው።

የነዳጅ ወይም የጥይት ማከማቻ መጋዘኖች ከተመቱ በኋላ ኃይለኛ ፍንዳታ እና ከፍተኛ እሳት መነሳቱን ምስሎች አሳይተዋል። ሩሲያ ብዙዎቹን ሰው አልባ አውሮፕላኖች መትታ መጣሏን ብትገልጽም የአካባቢው ባለስልጣናት በአየር ማረፊያው አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።

በሮስቶቭ፣ ኩርስክ እና ቤልጎሮድ ክልሎች የሚገኙ የነዳጅ ማከማቻ ቦታዎችም ኢላማ ተደርገዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው ሩሲያ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ከ600 በላይ ጋይድድ ቦምቦችን ወደ ዩክሬን ግዛቶች ከጣለች በኋላ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ተናግረዋል።

የሩስያ አውሮፕላኖችን ጥቃት እንዳይሰነዝሩ ዩክሬን ማገዷ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ይህን ለማድረግም የሩሲያ የአየር ማረፊያዎችን ማጥቃት "በጣም ፍትሃዊ ነው" ብለዋል።

የዩክሬን አጋሮች ቀደም ሲል ሩሲያ ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎችን በምዕራባውያን የጦር መሳሪያዎች እንድትመታ አልፈቀዱም ነበር። አሜሪካ ግን በቅርቡ በድንበር አካባቢ ያሉ አንዳንድ ኢላማዎችን እንድታጠቃ ለኪዬቭ ፍቃድ ሰጥታለች።