ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በምያንማር ታጣቂዎች እጅ የነበሩ 477 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ተመለሱ
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በምያንማር ታጣቂዎች እጅ የነበሩ 477 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር መመለሳቸውን የቤተሰቦች ኮሚቴ እና ተመላሾች ለቢቢሲ ተናገሩ።
በአካባቢው የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለቀሪዎቹ 300 ገደማ ኢትዮጵያውያን የአውሮፕላን ትኬት የመግዛት አቅም እንደሌላቸው በመግለጻቸው፤ ቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን መቼ እና እንዴት ሊመለሱ እንደሚችሉ እስከ አሁን እንዳልታወቀ ተገልጿል።
ከየካቲት ጀምሮ ለሦስት ወራት "ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ" (DKBA) እና "ቦርደር ጋርድ ፎርስ" (BGF) በተባሉ ሁለት ታጣቂዎች እጅ የቆዩት ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር መመለስ የጀመሩት ከሁለት ሳምንት በፊት ሚያዝያ 29/2017 ዓ.ም. ነበር።
ታይላንድ ውስጥ ጥሩ ክፍያ ያለው ሥራ እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸው ከሀገር የወጡት ኢትዮጵያውያን በታጣቂዎች እጅ ከመውደቃቸው አስቀድሞ የሳይበር ወንጀል በሚፈጸምባቸው ካምፖች ውስጥ ለግዳጅ ሠራተኝነት እና ለስቃይ ተዳርገው ነበር።
ካምፖቹ የሚገኙባቸውን አካባቢዎች የሚቆጣጠሩ ታጣቂዎች የካቲት ወር ላይ ተጎጂዎችን ማስወጣት የጀመሩ ሲሆን፣ የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን ደግሞ አምጸው በመውጣት በታጣቂዎች እጅ ገብተዋል። ሁለቱ ታጣቂዎች ኢትዮጵያውያኑን ጨምሮ ያስወጧቸውን የተለያዩ ሀገር ዜጎች በተለያዩ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ አስቀምጠዋል።
ሦስት ወራትን በመጠለያዎቹ ውስጥ ከቆዩት 751 ኢትዮጵያውያን መካከል ከግማሽ በላዩ በሁለት ሳምንት ውስጥ የተመለሱት በሕንድ ኒው ዴልሂ የሚገኘው ኤምባሲ የሀገሪቱን ዜጎች ምልሰት የሚያሳልጥ ተወካይ ወደ ታይላንድ መላኩን ተከትሎ ነው።
ኢትዮጵያውያኑ ጉዟቸውን የሚጀምሩት በምያንማር ከሚገኙት መጠለያዎች ወጥተው ወደ አጎራባቿ ታይላንድ በመሻገር ነው።
ወደ ታይላንድ ከገቡ በኋላ ደግሞ አየር ማረፊያ ወደሚገኝባት ዋና ከተማዋ ባንኮክ በአውቶብስ ይጓዛሉ። ለዚህ ጉዞ በአንድ ሰው 1,100 የአሜሪካ ዶላር ገደማ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ይህንን ወጪ የሸፈነው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው።
በዚህ መንገድ ከሚያዝያ 29 እስከ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ግንቦት 9/2017 ዓ.ም. ድረስ 477 ኢትዮጵያውያን መመለሳቸውን የቤተሰቦች ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበበች ሲመል እና ተመላሾች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በመጠለያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አስተባባሪ እና ከተመላሾች አንዱ የሆነው አዳነ ፍቅሬ እንደሚናገረው አሁን ከተመለሱት ተጎጂዎች መካከል 360 ገደማው ጊዜው ከአንድ ዓመት ያላለፈ መመለሻ የአውሮፕላን ትኬት የነበራቸው ናቸው።
120 የሚጠጉት ቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ጊዜው ያለፈበት ወይም ባመጧቸው ደላሎች የትኬቱ ገንዘብ ተመላሽ (refund) የተደረገባቸው ናቸው። እነዚህ ኢትዮጵያውያን የመመለሻ ትኬት የተቆረጠላቸው ታይላንድ ውስጥ በሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደሆነ አዳነ እና ወ/ሮ አበበች ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያኑን ለመመለስ ገንዘብ እያሰባሰቡ የነበሩት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች "ብዙ ትኬቶችን ቀጥታ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲገዙ 20 በመቶ ቅናሽ" እንደሚያገኙ እንደተገለጸላቸው ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ምንጮች፤ ትኬት ለሌላቸው ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የአውሮፕላን ትኬት ለመቁረጥ የሚያስችል ገንዘብ እንደሌላቸውም ገልጸው ነበር። ይህ የገንዘብ እጥረት አሁንም በታጣቂዎች መጠለያ ውስጥ ባሉት ኢትዮጵያውያን የመመለስ ጉዳይ ላይ ስጋት መፍጠሩን አዳነ እና ወ/ሮ አበበች ገልጸዋል።
ወ/ሮ አበበች፤ "ትኬት refund የተደረገባቸው ልጆች በጣም ብዛት አላቸው። እነሱን ማጓጓዝ ላይ የኢትዮጵያን መንግሥት ሊረዱ ቃል የገቡ ኤንጂኦዎች ትንሽ የማፈግፈግ ነገር ይታያል። 'አንዳንዴ 100 ሰው፣ 50 ነው የምንችለው፤ በጀት የለንም' ይላሉ" በማለት ተናግረዋል።
የወላጆች ኮሚቴ ተወካዮች ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች ጋር በነበራቸው ውይይት "ኤንጂኦ አልሸፍንም የሚል ከሆነ ለመንግሥታችን አቅርበን እናደርጋለን። እንጂ ማናቸውም መጠለያ ካምፕ ውስጥ አይቀሩም" የሚል ምላሽ እንዳገኙም ገልጸዋል።
ከዚህ ምላሽ ውጪ ቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን እንዴት እና መቼ እንደሚመለሱ እስካሁን አለመታወቁንም ያክላሉ።
ወ/ሮ አበበች፤ "[ታይላንድ ውስጥ በተወካይነት] የተመደበው ሰው ልጆቹን 'ከቅዳሜ በኋላ እቆያለሁ፤ ትኬት ቁረጡ' ይላቸዋል። አብዛኞቹ ደግሞ ትኬት የመቁረጥ አቅም የሌላቸው ከክፍለ ሀገር የመጡ፣ እዚያ መሆናቸውን እንኳ ቤተሰቦቻቸው የማያውቁ፣ የሚረዳቸው የሌላቸው ልጆች ናቸው" ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
በምያንማር የሚገኙት ኢትዮጵያውያን አስተባባሪ አዳነም ቀሪዎቹ ተጎጂዎች የሚመለሱበትን መንገድ በተመለከተ የተስፋ "ጭላንጭል እየታየ አይደለም" ሲል ስጋቱን ይጋራል። "የመንግሥት አንድ ተወካይ ልኮ ሂደቱን ጀምሮ፣ እኛን ወደ ሀገር ለመለስ ሦስት ወር ፈጅቶበታል።
"አሁን ደግሞ ለተቀሩት ልጆች [መመለሻ] 'በጀት የለም፣ ኤንጂኦዎች በጀት የላቸውም' የሚል ምክንያት [እየተሰጠ ነው]" ይላል።
በታይላንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ተወካይ 'ይመለሳል' የሚል ስጋት መኖሩንም ያክላል።
አዳነ እንደሚያስረዳው የኢትዮጵያውያንኑ ስጋት የሚመነጨው ወደ ሀገር የሚመለሱበት መንገድ ባለመታወቁ ብቻ ሳይሆን የሚቆዩበት መጠለያ ውስጥ ካሉት ችግሮች ጋር በተያያዘ ነው።
መጠለያዎቹ ንጽህና የጎደላቸው እንዲሁም የሚያገኙት ምግብ ከኢትዮጵያውያኑ "ባህል ጋር የሚቃረን" መሆኑን ይገልጻል።
ተጎጂዎቹ የሚተኙት በመጠለያው ህንጻ "ሴራሚክ ወለል" ላይ መሆኑን የሚናገረው አዳነ፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን "ለቆዳ በሽታ" መጋለጣቸውን ያስረዳል። "ኃይለኛ ሙቀት ያለበት አካባቢ ከመሆኑ የተነሳ እባብ አለ። [...] ሦስት ጊዜ የምንቀመጥበት ስፍራ ላይ እባብ አግኝተናል" ይላል።
አካባቢው ጦርነት ያለበት እንዲሁም ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱበት ከመሆኑም ጋር በተያያዘ "የእገታ" ስጋት መኖሩን ይናገራል። ከዚህ ቀደም አንድ ተጎጂ የታገተበት አጋጣሚ እንደነበረም ይጠቅሳል።
"አንድ ልጅ ታሞ መድኃኒት ለመግዛት በወታደር ታጅቦ በወጣበት አጋጣሚ፤ ሌላ BGF የሚባል አማጺ አግቶ ወስዶት በብዙ ችግር ነው ተለቆ የመጣው" ሲል በአካባቢው ያለው ኢትዮጵያውያንን አግቶ ለግዳጅ ሠራተኝነት የመሸጥ ልምድ የፈጠረውን ስጋት ገልጿል።
በበይነ መረብ ላይ ማጭበርበር የሚሠሩ ቡድኖች በደላሎች አማካይነት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ አገር ዜጎችን ሕጋዊ ሥራ እንሰጣለን በሚል ወደ ታይላንድ ከዚህም ወደ ምያንማር በመውሰድ ለስቃይ መዳረጋቸውን ቢቢሲ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ዘግቦ ነበር።
እነዚህ የተሻለ ሥራ እና ሕይወትን ፈለጋ ወደ ምያንማር የተወሰዱት ወጣቶች በኢንተርኔት አማካይነት በሚፈጸሙ ወንጀሎች እንዲሳተፉ ከመደረጋቸው በተጨማሪ ድብደባ እና ስቃይ እንደሚፈጸምባቸው ይናገራሉ።