ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊጉ የተሳካላቸው እና ውጤታማ ያልነበሩት አፍሪካዊያን ተጫዋቾች የትኞቹ ናቸው?

ቢሱማ፣ ሳላህ፣ ዊሳ እና ጃክሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ማንቸስተር ሲቲ ለተከታታይ አራተኛ ዓመት ሻምፒዮን ሆኖ ታሪክ የሠራበት የዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተጠናቋል።

ከዓመት በፊት ቡድኑ ዋንጫ ሲያነሳ ሪያድ ማህሬዝ ቁልፍ ተጫዋች ነበር። ዘንድሮ ግን ሲቲ አንድም አፍሪካዊ ተጫዋች አልነበረውም።

በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመት የትኞቹ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች ተሳካላቸው? እነማንስ የሚጠበቅባቸውን ይህል አልሆኑም? ሲል ቢቢሲ አፍሪካ ስፖርት ምርጫ አከናውኗል።

ከእነዚህ ተጫዋቾች መካል አንዳንዶቹ በሚቀጥለው ዓመት አዲስ ቡድን ፍለጋ ለገበያ ሲቀርቡ ሌሎቹ ደግሞ በአዲስ አሰልጣኝ ስር ይፎካከራሉ።

የተሳካላቸው

ዮአን ዊሳ (ብሬንትፎርድ)

ውጤታማ ባልነበረው የብሬንትፎርድ የውድድር ዓመት ዊሳ ያስቆጠራቸው 12 ጎሎች ቡድኑ ከሊጉ እንዳይወርድ እገዛ አድርገዋል።

በእንግሊዝ ቆይታው ምርጡን ውድድር ዓመት አሳልፏል። እንግሊዛዊው ኢቫን ቶኒ በቅጣት ብሪያን ምቡኤሞ ደግሞ በጉዳት አብዛኛውን ውድድር ዓመት ባይሰለፉም ዊሳ የቡድኑን የፊት መስመር በብቃት ምርቷል።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ወክሎ ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ካቀናበት ጊዜ ውጭ ለቡድኑ ግልጋሎት ያልሰጠበት ወቅት የለም።

አሁን የቡድኑ ወሳን ተጫዋች ለመሆን በቅቷል። ቶኒ በሚቀጥለው ዓመት ሊለቅ ይችላል የሚሉ ጭምጭምታዎች ከመበራከታቸው አንጻር የሚኖረው መሻሻል የሚታይ ይሆናል።

ኒኮላስ ጃክሰን (ቼልሲ)

ሴኔጋላዊው አጥቂ በቼልሲ የነበረው የመጀመሪያ ዓመት ወጥ አቋም ያሳየበት አልነበረም። በብዙ መልኩም የመሻሻል ዕድል አለው።

ጃክሰን በመጀመሪያዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ሁለት ጎሎችን ብቻ ነበር ያስቆጠረው። በኋላም ከተጣለበት ቅጣት በኋላ ሲመለስ ቶተንሃም ላይ ሃትሪክ አስቆጥሯል።

ብቃቱ ቢዋዥቅም ቡድኑ መጨረሻ ላይ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አራት ኳሶችን ከመረብ አገናኝቷል። ይህም ለወደፊት ኣለውን ተስፋ ያሳየ ሆኗል።

አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቸቲኖ በቡድኑ መቆየት እና ቼልሲ አዲስ አጥቂ የማስፈረሙ ጉዳይ የቀጣይ ዓመት ሚናውን የሚወስን ይሆናል።

ሞሐመድ ኩዱስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሞሐመድ ኩዱስ (ዌስት ሃም)

ጋናዊው ከአያክስ ከተዘዋወረ በኋላ ያለውን የማጥቃት አቅም ለማሳየት ችሏል።

ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው ሊጉ ተሳትፎው በጎሎች ለመታጀብ በቅቷል። ኳስ እና መረብ በማገናኘት የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ እየተቀመጠ ደስታውን የሚገልጽበት መንገድ ተደጋግሞ ታይቷል።

ጋናዊው ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ከቡድኑ ቢርቅም በውድድር ዘመኑ 14 ጎሎችን እና ስድስት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ለማመቻቸት ችሏል።

የዝውውር መስኮት ሲከፈት ትልልቅ ቡድኖች ሊወስዱት ፍላጎት ቢያሳዩ እንኳን ቡድኑ አሳልፎ የሚሰጠው አይመስልም።

አንቶኒ ሴሜንዮ (ቦርንመዝ)

ቦርንመዝ በአዲሱ አሰልጣኝ አንዶኒ አራኦላ ስር ብዙዎችን ያስገረመ አቋም አሳይቷል። ጋናዊው አጥቂ ሴሜንዮም ለዚህ ትልቅ ድርሻ ነበረው።

ፈጣኑ እና ተከላካዮችን እረፍት ሚነሳው አጥቂ የቡድኑ ቋሚ ተሰላፊ ለመሆንም በቅቷል።

ካስቆጠራቸው 10 ጎሎች አንጻር ቡድኑ ሴሜንዮን ከብሪስተል ሲቲ ለማዘዋወር ያወጣው 10 ሚሊዮን ፓውንድ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ተጫዋቹ ያለውን ጥንካሬ የሚያሳየው ደግሞ ለቡድኑ 33 ጊዜ ተሰልፎ ሲጫወት ለጋና ደግሞ 10 ጨዋታዎችን ማከናወኑ ነው።

የዚህ ዘርፍ ልዩ ተመራጮች. . .

ሳይመን አዲንግራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለፈው ዓመት በውሰት ቤልጂየም ቆይቶ የተመለሰው ሳይመን አዲንግራ ለቡድኑ ብራይተን ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ጎል ከማስቆጠሩም በላይ በውድድር ዓመቱ ስድስት ኳሶችን ከመረብ አገናኝቷል።

የ22 ዓመቱ ተጫዋች ድንቅ ብቃት የታየው የአይቮሪ ኮስት ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ባለድል ስትሆን ጎል አስቆጥሮ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ባመቻቸበት ውድድር ነው።

ኤቨርተን መጋቢት ላይ 13 ጨዋታዎችን ሳያሸንፍ ባደረገው ጉዞ ከሊጉ ሊወርድ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሮ ነበር።

በዚህ ወቅት ብቅ ያለው ያልታሰበው ኮከብ ደግሞ ኢድሪሳ ጋና ጉዬ ነው። በውድድር ዘመኑ ማብቂያ ላይ ቡድኑ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አማካዩ ሦስት ጎሎችን አስቆጥሯል።

የዘንድሮው ውድድር ዓመት ለራያን አይት-ኑሪ የተለየ ነበር። ለአልጄሪያም ሆነ ለዎልቭስ ቋሚ በመሆን መጫወት የጀመረበት ዓመት።

የግራ መስመር ተከላካዩ ወደ ፊት ሲሄድ ያለው የማጥቃት አቅም ከማንቸስተር ሲቲ፣ አርሰናል እና ሊቨርፑል ጋር ስሙ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።

ያልተሳካላቸው

ሞሐመድ ሳላህ (ሊቨርፑል)

ዘንድሮ በሊጉ ከሚገኙ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች 18 ጎሎችን በማስቆጠር ቀዳሚ የሆነው ሞሐመድ ሳላህ ባልተሳካላቸው ዝርዝር ውስጥ መካተቱ ሊያስገርም ይችላል።

ካለፉት ሰባት ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ ያስቆጠረው አጥቂው በ2017 ሊቨርፑልን ከተቀላቀለ በኋላ በዝቅተኛ የጎል መጠን የውድድር ዓመቱን ለማጠናቀቅ ተገዷል።

በአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ያስተናገደው ጉዳት ሊቨርፑል አሸናፊ ከሆነበት የካርሊንግ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ውጭ እንዲሆን አስገድደቶታል።

ቀጥሎ ቡድኑ ከዩሮፓ የሩብ ፍጻሜ ለመባረር ተገደደ። ቡድኑ ለዋንጫዎች ያለው ተስፋ በተመናመነበት ወቅት አጥቂው ከአሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ጋር በይፋ አለመግባባት ውስጥ ገባ።

አርን ስሎት አዲስ አሰልጣኝ ሆነው ለሊቨርፑል ተሹመዋል። ቡድኑ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎንም አረጋግጧል። ሳላህስ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ወደ ሌላ ክለብ ያማትር ይሆን?

ቢሱማ (ቶተንሃም)

ቶተንሃም የውድድር ዓመቱን በአዲሱ አሰልጣኝ አንጅ ፕስትኮግሉ ስር ሆኖ ጀምሯል። ካሳየው ድንቅ አጀማር በተጨማሪ በሊጉ አናት ላይ እስከመቀመጥ ደርሶ ነበር።

ቀጥሎም ቡድኑ አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ድል ማስመዝግብ ሳይችል ቀረ። ቢሱማ በውድድር ዓመቱ ባየው ሁለተኛ ቀይ

ሦስት ጨዋታዎችን ተቀጣ።

በአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ተጫዋቹ በወባ በመያዙ ምክንያት አቋሙ ወረደ። ቡድኑም የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን ሳይችል ቀረ።

ቢሱማ የመጨረሻዎቹን ሁለት የሊጉን ጨዋታዎች በጉልበት በጉዳት ሳይሰለፍ ቀረ። ማሊ በቀጣይ ለ2026 የዓለም ዋንጫ ከምታደርገው ማጣሪያ ጨዋታዎች ውጭም ሆነ።

ሶፍያን አምራባት (ማንቸስተር ዩናይትድ)

ሶፍያን አምራባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሞሮኮ በዓለም ዋንጫ ላይ እስከ ግማሽ ፍጻሜ ባደረገችው ታሪካዊ ጉዞ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ተጫዋች የማንቸስተርን የማካይ ስፍራ ይቀይረዋል በሚል ትልቅ ተስፋ ከፊዮረንቲና በውሰት እንግሊዝ ደረሰ።

ክለቡ ደካማ አቋም ባሳየበት የውድድር ዓመት የ27 ዓመቱ ተጫዋች አስር ጨዋታዎች ላይ ብቻ በቋሚነት ተሰለፈ።

የኤሪክ ቴን ሃግ ቡድን ከአውሮፓ መድረክ በጊዜ ተሰናበተ። ብዙ ግምት የተሰጠው የሞሮኮ ቡድን በደቡብ አፍሪካ ከጥሎ ማለፉ ውጭ ሲሆን አምራባት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወገደ።

ማንቸስተር ዩናይትድ በሚቀጥለው ዓመት በአውሮፓ መድረክ የመሳተፉ ነገር በኤፍኤ ካፕ ዋንጫ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በሚያደርገው የፍጻሜ ጨዋታ ይወሰናል። ቡድኑ 17 ሚሊዮን ፓውንድ ከፍሎ የአምራባትን የውሰት ውል ቋሚ የማድረጉ ጉዳይም ገና ውሉ አልየም።

ኢሳ ካቦሬ (ሉተን ታወን)

በውሰት ከማንቸስተር ሲቲ ወደ ሉተን ያቀናው የ23 ዓመቱ ተጫዋች ብዙዎች እንደገመቱት ሊሳካለት አልቻለም። ውድድር ዘመኑ በአፍሪካ ዋንጫ እና በጉዳት እንከን እንደገጠመው ማሰብም ይገባል።

ካቦሬ 21 ጨዋታዎችን በቀኝ የተመላላሽ ቦታ ላይ ጀምሮ ሁለት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አቀብሏል። ቡድኑን ግን ከመውረድ አላስቻለም።

ተጨዋቹ ወደ ሊጉ አሸናፊ እናት ቡድኑ የሚመለስ ቢሆንም በሲቲ ያለው ቆይታ ግን ጥርጣሬ ውስጥ ገብቷል።

የዚህ ዘርፍ ልዩ ተመራጮች. . .

ኢብራሂም ሳንጋሬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማንቸስተር ዩናይትድ ባለፈው ክረምት 47.2 ሚሊዮን ፓውንድ በማውጣት ግብ ጠባቂውን አንድሬ ኦናናን ከኢንተር ሚላን አስፈርሟል። የግብ ዘቡ ጠንካራም ሆነ ደካማ ውድድር ዓመት አሳልፏል ለማለት ይከብዳል።

ዓመቱን ሙሉ በጉዳት ሲቀያየር በነበረው የተካላካይ መስመር ይህ ነው የሚባል እገዛ ሳያገኝ ዘጠኝ ጨዋታዎች ላይ ጎሉን ሳያስደፍር ወጥቷል። በዚህ ረገድ የማንቸስተር ሲቲው ኤደርሰን በአንድ ጨዋታ ብቻ ይበልጠዋል። ግብ ጠባቂው ዋጋ ያስከፈሉ ስህተቶችን መሥራቱ ግን አይካድም።

ካሜሮን የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዋን በምታደርግበት ዕለት ወደ ውድድሩ ስፍራ ማቅናቱም በበጎ አልታየም። በውድድሩም አንድ ጨዋታ ብቻ በቋሚነት ጀምሯል።

የአይቮሪ ኮስቱ ኢብራሂም ሳንጋሬ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሻለ ጊዜ አሳልፏል። ቡድኑ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች በስድስቱ ተሳትፏል። ከፒኤስቪ ወደ ኖቲንግሃም ፎረስት ከተዘዋወረበት 30 ሚሊዮን ፓውንድ አንጻር ግን ለቡድኑ ያበረከተው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

በርካታ ችግሮች በነበሩት ቡድን ውስጥ 13 ጨዋታዎች በቋሚነት ተሰልፎ ጀምሯል። ጎልም ሆነ ለጎል የሚሆነወ ኳስ ግን ማቀበል አልቻለም።

ሼፊልድ ዩናይትድ ሦስት አፍሪካዊያን ተጫዋቾችን ከውድድር ዓመቱ ጅማሮ በፊት አስፈርሟል። እንደቡድኑ ሁሉ ተጫዋቾቹም አመርቂ ነገር አላሳዩም።

በውሰት የመጣው አልጄሪያዊው ያሽር ላሩቺ ስድስት ጨዋታዎችን ብቻ በቋሚነት ጀምሯል። የወረደው ቡድን የተጫዋቹን የውሰት ውል ወደ ቋሚነት የመቀየር ፍላጎት ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም።