ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
3 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የተሰረቀ ቢትኮይን በፈንድሻ ጣሳ ተገኘ
የዩናይትድ ስቴትስ የፍትህ ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት ታዋቂ ከሆነ ዳርክኔት ድረገጽ የተሰረቀ 3.36 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን መያዙን ገልጿል።
50,676ቱ የቢትኮይን ክምችት የፈንዲሻ ጣሳን ጨምሮ በተለያዩ ቁሶች ላይ ተደብቆ በአንድ መረጃ መንታፊ ቤት ከመሬት በታች በሚገኝ መደበቂያ ተገኝቷል።
ጀምስ ዞንግ እአአ በ2012 ገንዘቡን ከህገ-ወጡ ሲልክ ሮድ በመመንተፍ ጥፋተኛ ነኝ ብሏል።
የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት እንደተናገሩት የተያዘው መጠን በትልቅነቱ በታሪክ ሁለተኛው ነው።
በጆርጂያ የሚገኘው የዞንግ መኖሪያ ቤት በፖሊስ የተበረበረው ከአንድ ዓመት በፊት ቢሆንም ይፋ የተደረገው አሁን ነው።
የቢትኮይን ዋጋ እያሻቀበ በመጣበት በዚህ ወቅት የተያዙት ገንዘቦች አሁን ባለው ዋጋ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ያህል ያወጣሉ።
ፖሊስ እንዳለው ዞንግ ገንዘቡን ከሲልክ ሮድ ለመስረቅ የቻለው በድረ-ገጹ የክፍያ ስርዓት ያለውን ክፍተት በመጠቀም ነው።
መስከረም 2012 ዳርክኔት ላይ ብዙ አካውንቶችን በመክፈት አነስተኛ መጠን ያለው ቢትኮይን አስቀመጠ። ከዚያም ጥርጣሬን ላለመፍጠር በጣም ብዙ መጠን በፍጥነት ለማውጣት መንገድ አገኘ ይላል ፖሊስ።
ሲልክ ሮድ ከ2011 እስከ 2013 አካባቢ የሠራ የመጀመሪያው ዳርክኔት የተሰኘ የግብይት ስፍራ ነበር። በዕጽ አዘዋዋሪዎች እና ሌሎች ሕገወጥ ሻጮች ከፍተኛ ሕገወጥ መድኃኒቶችንና ሌሎች ሕገወጥ ዕቃዎችን እና አገልግሎቶችን ለገዥዎች ለማከፋፈል ይጠቀምበት ነበር።
ዳርክኔት ልዩ ሶፍትዌርን በመጠቀም ብቻ ሊደረስበት የሚችል የበይነመረብ ዓይነት ነው።
የሲልክ ሮድ መስራች ሮስ አልብሪች እአአ በ2015 ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።
ዞንግ ድረ ገጹን በመጥለፍ ጥፋተኛ ነኝ ብሎ ከማመመን ባለፈ ቢትኮይኖቹን እና ንብረቶቹን ለፖሊስ አሳልፎ በመስጠት እና የቅጣት ውሳኔውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስራት ይጠብቀዋል ተብሏል።
የህግ ባለሙያው ዴሚያን ዊልያምስ እንዳሉት ፖሊስ ቢትኮይኑን ለማግኘት ክሪፕቶ ከረንሲ መከታተያ ዘዴዎችን ተጠቅሟል።
"ለ10 ዓመታት ያህል፣ ይህ ግዙፍ ቢትኮይን የጠፋበት ቦታ የ3.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ምስጢር አካል ሆኖ ቆይቷል” ብለዋል።
"ይህ ጉዳይ የፈንድሻ ጣሳን ጨምሮ ምንም ያህል የተደበቀ ቢሆንም መከታተላችንን እንደማናቆም ያሳያል።"
በጊዜው ይህ በአሜሪካ ታሪክ ትልቁ የክሪፕቶከረንሲ ዘርፍ የተያዘ ነው። ከ2016 የቢትፊኔክስ ጠለፋ ከተሰረቀ ቢትኮይን በየካቲት ወር የተያዘው ከ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲወረስ ግን ብልጫውን ለመያዝ ችሏል።