የጋዛ ባለሥልጣናት በእስራኤል ጥቃት ሕጻናት መገደላቸውን ሲገልፁ መከላከያው 'በስህተት' መሆኑን አመነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እሁድ ዕለት በማዕከላዊ ጋዛ ውሃ ለመቅዳት በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ስድስት ሕጻናትን ጨምሮ፣ አስር ሰዎች በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደላቸውን የድንገተኛ አገልግሎት ባለሥልጣናት ገለፁ።
የሟቾቹ አስከሬን ወደ ኑሴይራት አል አውዳ ሆስፒታል የተላከ ሲሆን ሰባት ሕጻናትን ጨምሮ 16 የተጎዱ ሰዎችንም ማከማቸውን አንድ ዶክተር ተናግረዋል።
በአል ኑሴይራት የስደተኞች መጠለያ ካምፕ የውሃ ማጠራቀምያ አጠገብ ባዶ ጀሪካን ይዘው በተሰለፉ ሰዎች ላይ አንድ ድሮን ሚሳኤል መተኮሱን የዓይን እማኞች ተናግረዋል ።
የእስራኤሉ ጦር እስላማዊ ጂሃድ "አሸባሪ" ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በሚፈጸምበት ወቅት "የቴክኒክ ስህተት" ማጋጠሙን ተናግሯል።
በዚህም የተነሳ ተተኳሹ ከታቀደው ስፍራ በርካታ ሜትሮች ርቆ ሊወድቅ ችሏል ሲል ማብራርያ ሰጥቷል።
የእስራኤል መከላከያ ክስተቱን እየገመገመ መሆኑንም አስታውቋል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት "በዚህም ምክንያት በአካባቢው የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ የቀረበውን መረጃ እናውቃለን" ብሏል። የዜጎችን ጉዳት "በተቻለ መጠን" ለመከላከል እንደሚሰራ እና "በግጭት ውስጥ ያልተሳተፉ ሰላማዊ ዜጎች ላይ በሚደርስ ማንኛውም ጉዳት እንደሚጸጸት" ተናግሯል።
ትክክለኛነቱ በቢቢሲ የተረጋገጠ ጥቃቱን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል፤ በርካታ ሰዎች ተጎጂዎችን ለመርዳት ሲሯሯጡ እና ሕጻናት በቢጫ ጀሪካኖች መካከል ወድቀው አሳይቷል።
ቢቢሲ ቬሪፋይ ጥቃቱ የተፈፀመበትን ትክክለኛ ስፍራ ማመልከት ችሏል።
በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ጥቃቱ የተፈጸመው ማለዳ ላይ መሆኑን ከተንቀሳቃሽ ምስሉ መረዳት ይቻላል።
ጥቃቱ ከኑሴይራት መካከለኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በስተደቡብ ምዕራብ 80ሜ መንገድ ላይ መፈጸሙንም በአካባቢው የሚገኙ መኖርያዎች እና ዛፎችን በመመልከት ማወቅ ተችሏል።
ይህ ስፍራ ከሁለት ሕንጻዎች ባሻገር በኦንላይን መዋዕለ ሕጻናት መሆኑ ከተገለፀ ሕንጻ አቅራቢያ የሚገኝ ነው።
ከሦስት ሳምንት በፊት የተቀረፁ የሳተላይት ምስሎች ከመንገዱ ባሻገር የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር ቆሞ ያሳያሉ።
ቪዲዮው ላይ ጣቢያውን ምን እንደመታው እንዲሁም በስህተት የተወነጨፈ የእስራኤል ሚሳዔል መሆን አለመሆኑ እና ከየት አቅጣጫ እንደተተኮሰ ማወቅ አይቻልም።
ጥቃቱ የደረሰው በጋዛ ሰርጥ የእስራኤል የአየር ጥቃት እየከፋ በመጣበት ወቅት ነው።
የጋዛ ሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ እንዳስታወቁት እሁድ ዕለት በማዕከላዊ ጋዛ እና በጋዛ ከተማ በሚገኙ የመኖሪያ ሕንፃዎች ላይ በተፈፀሙ ጥቃቶች 19 ሌሎች ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
በሌላ ዜና ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ባለፉት ስድስት ሳምንታት በደቡባዊ ጋዛ በሚገኘው ራፋህ መስክ ሆስፒታል ውስጥ ከዚያ በፊት ከነበሩት 12 ወራት በበለጠ በጅምላ የተጎዱ ሰዎችን ማከሙን ገልጿል።
በራፋ የሚገኘው የመስክ ሆስፒታሉ ቅዳሜ ዕለት 132 ቁስለኞችን "ከመሳሪያ ጋር በተያያዙ ጉዳቶች" ማከሙን ገልፆ፣ ከእነዚህም ውስጥ 31ዱ ሞተዋል ብሏል።
"አብዛኞቹ" ታማሚዎች በጥይት መቁሰላቸው እና "ሁሉም ስለ ጉዳታቸው የተናገሩ ግለሰቦች" የምግብ ማከፋፈያ ቦታዎች ለመሄድ ሲሞክሩ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ እ.አ.አ በግንቦት 27 አዳዲስ የምግብ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ከተከፈቱ በኋላ ከ3,400 በላይ በጦር መሳሪያ የተጎዱ ታካሚዎችን ማከሙን እና ከ 250 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ገልጾ፣ ይህ ቁጥር ባለፈው ዓመት "በሆስፒታል ከታከሙ የጅምላ አደጋዎች" ሁሉ ይበልጣል ብሏል።
አይሲአርሲ "የእነዚህ የጅምላ ጉዳት አደጋዎች አስደንጋጭ ድግግሞሽ እና መጠን በጋዛ ውስጥ ያሉ ሰላማዊ ዜጎች የሚኖሩበትን አሰቃቂ ሁኔታዎች አጉልቶ ያሳያል" ሲል ገልጿል።
ቅዳሜ ዕለት በደቡባዊ ጋዛ ናስር ሆስፒታል በእርዳታ ማከፋፈያ ቦታ 24 ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ገልፀው፣ ምግብ ለማግኘት ሲሞክሩ የእስራኤል ወታደሮች ተኩስ እንደከፈቱባቸው አስረድተዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) በጣቢያው አቅራቢያ በነበረው ተኩስ "የተጎዱ ሰዎች አልታወቁም" ብሏል።
እስራኤል እ.አ.አ ጥቅምት 7/2023 በሐማስ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት 1,200 ሰዎች መገደላቸውን እና 251 ሰዎች መታገታቸውን ተከትሎ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታለች።
እንደ ሐማስ መራሹ የጤና ሚኒስቴር መረጃ በጋዛ እስካሁን ቢያንስ 57,882 ሰዎች ተገድለዋል።















