በእርዳታ ጣቢያ አቅራቢያ 24 ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ ሆስፒታል ሲያሳውቅ የዓይን እማኞች የእስራኤል ጦርን ወነጀሉ

እርዳታ ጣቢያ ላይ የተገደለ ልጃቸው ሀዘን ላይ የተቀመጡ እናት ከሌላ ልጃቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, እርዳታ ጣቢያ ላይ የተገደለ ልጃቸው ሀዘን ላይ የተቀመጡ እናት ከሌላ ልጃቸው ጋር
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በደቡባዊ ጋዛ የሚገኘው ናስር ሆስፒታል በእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያ አቅራቢያ 24 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

በእርዳታ ማከፋፈያው የነበሩ ፍልስጤማውያን ቅዳሜ ዕለት ምግብ ለመቀበል ሲሞክሩ የነበሩ ሰዎች ላይ የእስራኤል ወታደሮች ተኩስ መክፈታቸውን ተናግረዋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) በጣቢያው አቅራቢያ በነበረው ተኩስ "የተጎዱ ሰዎች አልታወቁም" ብሏል።

ከዚህ በተናጠል አንድ የእስራኤል ጦር ባለስልጣን መከላከያ ኃይሉ ስጋት ናቸው ብሎ ያመናቸው ሰዎችን ለመበተን የማስጠንቀቂያ ተኩስ መተኮሶን ተናግረዋል።

በሁለቱም ወገኖች የቀረቡ ክሶች በገለልተኛነት የተረጋገጡ አይደሉም። እስራኤል ቢቢሲን ጨምሮ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ጋዛ እንዲገቡ አትፈቅድም።

በቢቢሲ የታየ ተንቀሳቃሽ ምስል በናስር ሆስፒታል ቅጥር ግቢ በርካታ አስከሬኖች ተጠቅልለው ደም የተለወሰ አልባሳት በለበሱ ሐኪሞች እና ነርሶች ተከበው ተመልክቷል።

በሌላ ተንቀሳቃሽ ምስል አንድ ግለሰብ ሰዎች እርዳታ ለማግኘት እየተጠባበቁ እያለ ለአምስት ደቂቃ ያህል ተኩስ እንደተከፈተባቸው ይናገራሉ።

አንድ የጤና ባለሙያ የእስራኤል ወታደሮች በጭካኔ ግድያውን ፈፅመዋል ሲል ከሷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ነገር ግን ተንቀሳቃሽ ምስሎቹ በቢቢሲ አልተረጋገጡም።

ሮይተርስ ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች ሰዎች ግንባራቸውን እና ከእግራቸው በላይ መመታታቸውን ገልፀዋል።

የዜና ወኪሉ በናስር ሆስፒታል በነጭ ጨርቅ የተጠቀለሉ አስከሬኖችን መመልከቱንም ዘግቧል።

በጋዛ ምግብ ለማግኘት በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ የእስራኤል ወታደሮች የሚከፍቷቸው ተኩሶች በየቀኑ እየተዘገቡ ነው።

ከመጋቢት ወር ጀምሮ እስራኤል ለጋዛ የሚደርስ የእርዳታ አቅርቦት ላይ እግድ በመጣል በሐማስ የምታደርገውን ጥቃት ዳግም በመጀመር የሁለት ወር የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሳለች።

አገሪቱ የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን የእስራኤልን ታጋቾች እንዲለቅ ጫና ለማሳደር መፈለጓን ተናግራለች።

ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ረሃብ ማንጃበቡን ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ ባለፈው ግንቦት እግዱ በከፊል ላላ ቢልም ከፍተኛ የምግብ እንዲሁም የመድኃኒት እና ነዳጅ እጥረት አለ።

የመንግሥታቱ ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጄንሲ በአካባቢው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት በምግብ እጥረት የተጎዱ መሆናቸውን እና ሁኔታው በየቀኑ እየተባባሰ ነው ብሏል።

ከጥቂት የመንግሥታቱ ድርጅት የእርዳታ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ እስራኤል እና አሜሪካ ሐማስ እርዳታውን እንዳይሰርቅ በሚል 'ጋዛ ሂውማኒቴሪያን ፋውንዴሽን' በተባለ ተቋማ አማካኝነት የእርዳታ ማሰራጫ ስርዓት ዘርግተዋል።

አርብ ዕለት የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ ከእርዳታ ጋር የተያያዘ 798 የሰዎች ግድያ መመዝገቡን ገልጿል። ከዚህ ውስጥ በአሜሪካ የግል የደኅንነት ተቀጣሪ በሚጠበቀው እና በወታደራዊ ክልል ውስጥ በሚገኘው በ'ጋዛ ሂውማኒቴሪያን ፋውንዴሽን' ጣቢያ አካባቢ የተገደሉት 615ቱ ናቸው።

ሌሎቹ 183 ሰዎች የተገደሉት በተመድ እና በሌሎች የእርዳታ ስፍራዎች ነው።

የእስራኤል መከላከያ ንፁኃን ሰዎች የተጎዱባቸው አንዳንድ ክስተቶች እንዳሉ እውቅና ሰጥቶ፤ "በሕዝቡ እና በእስራኤል ኃይል መካከል በተቻለ መጠን ሊፈጠር የሚችል ግጭት" ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

'ጋዛ ሂውማኒቴሪያን ፋውንዴሽን' የመንግሥታቱ ድርጅት ከሐማስ ከሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር "የውሸት እና አሳሳች" መረጃዎችን እየተጠቀመ ነው ሲል ከሷል።

በዚህ ወር መጀመሪያ የፋውንዴሽኑ የቀድሞ የደኅንነት ቅጥረኛ፤ ባልደረቦቹ ምንም ስጋት ባልደቀኑ ረሃብተኛ ፍልስጤማውያን ላይ በርካታ ጊዜ ተኩስ መክፈታቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ፋውንዴሹኑ የቀረበበትን ክስ ውሸት ብሏል።

እስራኤል እ.አ.አ ጥቅምት 7/2023 በሐማስ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት 1,200 ሰዎች መገደላቸውን እና 251 ሰዎች መታገታቸውን ተከትሎ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታለች።

እንደ ሐማስ መራሹ የጤና ሚኒስቴር መረጃ በጋዛ እስካሁን ቢያንስ 57,823 ሰዎች ተገድለዋል።