ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕ በመወለድ የሚገኝ ዜግነት የማስቀረት ውሳኔያቸውን ለማገድ ዳኞች የሚኖራቸውን ሥልጣን ገደበ
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የስር ፍርድ ቤቶች ፕሬዚደንታዊ ትዕዛዛትን ለማገድ የሚያስችላቸው ሥልጣን ውስን እንዲሆን በየነ።
ይህም ፕሬዚደንት ትራምፕ "ትልቅ ድል" ያሉትን እድል ሰጥቷቸዋል።
ውሳኔው ትራምፕ ዜጋ ካልሆኑ እና ሕጋዊ ሰነድ ከሌላቸው ስደተኞች የሚወለዱ ልጆች፣ አሜሪካ ውስጥ በመወለድ ዜግነት እንዳያገኙ ለማድረግ ፕሬዚደንታዊ ትዕዛዝን ከመጠቀማቸውን ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው።
6ለ 3 በሆነ ድምጽ ውሳኔውን ያሳለፉት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ወግ አጥባቂ ዳኞች በውሳኔያቸው ትራምፕ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን ለማስቆም የሚያደርጉትን ሙከራ እያገዙ እንዳልሆነና ውሳኔው ፕሬዚደንታዊ እርምጃዎችን በስፋት የተመለከተ እንደሆነ ገልጸዋል።
ባለሙያዎች ግን ውሳኔው ወደፊት የሥራ አስፈፃሚ እርምጃዎችን የመገዳደር ሒደትን እንደሚለውጥ በመግለጽ አርብ እለት በነበረው ውሳኔ ላይ ሕጋዊ ጥያቄዎች መነሳታቸው እንደማይቀር ተናግረዋል።
የስደተኞች መብት ተቆርቋሪ ቡድኖች እና 22 ግዛቶች ፕሬዚደንት ትራምፕ ወደ ዋይት ሃውስ በተመለሱ በመጀመሪያው ቀን ባስተላለፉት ትዕዛዝ አስተዳደራቸውን ከሰዋል።
ትዕዛዙ ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ውስጥ የሚወለዱ ልጆች ወዲያውኑ ዜግነት ማግኘት የሚያስችላቸውን ሕግ የሚሽር እና በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን የሚከለክል ነው።
ይህንንም ተከትሎ በሜሪላንድ፣ ማሳቹሴትስ፣ ዋሽንግተን እና ሌሎች ግዛቶች ፕሬዚደንታዊ ትዕዛዙ ተግባራዊ እንዳይሆን ያለመ ክስ ያቀረቡ ሲሆን ለጊዜው ቢሆን እርምጃውን ማስቆም ችለዋል።
ሆኖም የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ " ውሳኔዎቹ ሕገ መንግሥታዊ አይደሉም" ሲል ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ብሏል።
ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤትም አርብ ዕለት የፌደራል ፍርድ ቤቶች በሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዛት ላይ ውሳኔ ለማስተላለፍ የሚያስችላቸውን ሥልጣን ገድቧል።
ትራምፕ አርብ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ውሳኔውን እንደ "ድል" እንደቆጠሩት ገልጸው፤" ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሥልጣን ክፍፍል እና ለሕገ የበላይነት ወሳኝ ድል ነው" ብለዋል።
ትራምፕ ጨምረውም 'ጽንፈኛ' ዳኞች ፕሬዚደንታዊ ሥልጣናቸውን ለመሻር እንደሞከሩ ጠቅሰው፤ " እንዲህ ያሉ እርምጃዎች ለዴሞክራሲ ትልቅ እንቅፋት" መሆናቸውን ተናግረዋል።
ትራምፕ ባለፈው ጥር ወር ላይ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸው ወደ ዋይት ሃውስ ከተመለሱ በኋላ አጀንዳዎቻቸውን ለማስፈፀም የሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዛትን መጠቀም ጀምረዋል።
ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲም ውሳኔው ዳኞች የትራምፕን ፖሊሲዎች ማስቆም እንደማይችሉ የሚያሳዩ መሆናቸውን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጥቅምት ወር ላይ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን የተመለከቱ ጥያቄዎችን ይቀበላል ብለው እንደሚጠብቁም ፖም ተናግረዋል።
አርብ ዕለት በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተላለፈው ውሳኔ ፍርድ ቤቶች አሁንም ቢሆን ኢ- ሕገ መንግሥታዊ እና ሕገ ወጥ ነው ያሉትን ፕሬዚደንታዊ ትዕዛዛት ማስቆም እንደሚችሉ ቢገልጽም ፕሬዚደንቶች እርምጃ እንዲወስዱ በር ይከፍታል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው መሰረት የትራምፕ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን የሚከለክለው ትዕዛዝ በፍርድ ቤቱ አስተያየት ከቀረበበት ከ30 ቀናት በኋላ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።
ሆኖም ውሳኔው የሕግ ጥያቄዎች ሊገጥሙት ይችላሉ።
በኖተርዳም የሕግ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት ሳሙኤል ብሬይ እንዳሉት ውሳኔው በፌደራል ፍርድ ቤቶች እና በሥራ አስፈፃሚው አካል መካከል ያለውን ግንኙነት በመሰረታዊነት የለወጠ ነው ብለዋል።
የብዙሃኑን አስተያየት የጻፉት ዳኛ ኤሚይ ኮኒይ በበኩላቸው የፌደራል ፍርድ ቤቶች በሥራ አስፈፃሚው አካል ላይ አጠቃላይ ቁጥጥር እንደማያደርጉ እና ምክር ቤቱ ከሰጣቸው ሥልጣን ጋር ብቻ የሚጣጣሙ ጉዳዮችን እና ውዝግቦችን እንደሚፈቱ ገልጸዋል።
" አንድ ፍርድ ቤት የሥራ አስፈፃሚው አካል ሕገ ወጥ ድርጊት ፈፅሟል ብሎ ሲደምድም የሚሰጠው ብይን ከሥልጣኑ መብለጥ የለበትም" ብለዋል።
ተመሳሳይ አስተያየት የጻፉት ዳኛ ብሬትም በዋና ዋና የፌደራል ሕጎች እና ሥራ አስፈፃሚዎች ትዕዛዛት ሕጋዊ ሁኔታን በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጡት የግዛት ፍርድ ቤቶች ወይም የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ሳይሆኑ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ነው የሚሆነው ብለዋል።
የሊበራል ዳኛው ሶንያ ሶቶሜየር ግን የትራምፕ አስተዳደር ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ጥያቄ " የሚያሸንፉበት ጨዋታ ነው፤ ፍርድ ቤቱም አብሮ እየተጫወተ ነው" ሲሉ ውሳኔውን ተቃውመዋል።
" የፍርድ ቤቱ ውሳኔ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን እንዲጥስ ግብዣ ከማቅረብ አይተናነስም" ብለዋል።
"የሕግ የበላይነት ዝም ብሎ የተሰጠ አይደለም። በየዘርፉ ያሉ ሁሉ ለህልውና ሲታገሉ ብቻ የሚፀና ነው። ዛሬ ፍርድ ቤቱ በዚህ ላይ ያለውን ሚና ጥሎታል። ፕሬዚደንቱም በሕገ መንግሥታችን ላይ አላግጠዋል" ብለዋል ዳኛ ሶንያ።