ፑቲን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳይጠቀሙ ባይደን አስጠነቀቁ

ታትሟል

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሩሲያ የኬሚካልም ይሁን የታክቲካል ኒውክሌር ጦር መሣሪያ በዩክሬን ጦርነት ላይ እንዳትጠቀም አስጠነቀቁ።

ባይደን ከሲቢኤስ ቴሌቪዥን ጋር ባረደጉት ቆይታ የኒውክሌር መሣሪያ መጠቀም “ጦርነትን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ባልታየ ሁኔታ ይቀይረዋል” ብለዋል።

የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ ቢውል አገራቸው ምን እርምጃ እንደምትወስድ ግን የገለጹት ነገር የለም።

ከዩክሬን ጦርነት ወዲህ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአገራቸውን የኒውክሌር ኃይል “በተጠንቀቅ” እንዲቆም ማዘዛቸው ይታወሳል።

ይህንን ያደረጉት “ከምዕራቡ ዓለም ማስፈራሪያዎች” ስለሚወጡ እንደሆነ ገልጸዋል።

ላለፉት 80 ዓመታት ዓለም ላይ የቆዩትን የኒውክሌር መሣሪያዎች አንዳንድ አገራት እንደ ደኅንነታቸው ማረጋገጫ ይቆጥሯቸዋል።

የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ፌደሬሽን እንደሚለው ሩሲያ 5,977 ገደማ ከኒውክሌር ኃይል ጋር የተያያዙ መሣሪያዎች አሏት።

መሣሪያዎቹን ትጠቀማለች ተብሎ ግን አይጠበቅም።

ታክቲካል ኒውክሌር በመባል የሚታወቁት የአጭር ርቀት መሣሪያዎች ሲሆኑ፣ ስትራቴጂክ ኒውክሌር ደግሞ የረዥም ርቀት ተስወንጫፊ መሣሪያዎችን ያካትታል።

ፑቲን የኒውክሌር መሣሪያ በዩክሬን ለመጠቀም አስበው ከሆነ ምን መልዕክት ማስተላለፍ ይፈልጋሉ ተብለው በሲቢኤስ የተጠየቁት ባይደን “ተው! ተው! ተው!” ሲሉ መልሰዋል።

አሜሪካ የኒውክሌር ጥቃትን ተከትሎ ምን እርምጃ እንደምትወስድ በግልጽ ባይናገሩም “ዓለም ላይ ታይተው ከሚታወቁ ቀውሶች ሁሉ የባሰ ይሆናል። የሚከሰተውን ጉዳት ያህልም ምላሽ እንሰጣለን” ብለዋል።

በአጠቃላይ ዩክሬን ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ8 ሺህ ካሬ ኪሎሜትር (800 ሺህ ሄክታር) በላይ የሚሆን ግዛት ከሩሲያ መልሳ እንደገና መቆጣጠሯን ገልጻለች። ይህም ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶም ዩክሬን ያስመዘገበችው ከፍተኛ ስኬት ነው ተብሏል።

ፑቲን በበኩላቸው የዩክሬን የቅርብ ጊዜ ድል ኦፕሬሽናቸውን እንደማይገታው ተናግረዋል።