የሁቲ አማጽያን የሚሳኤል ጥቃት የአሜሪካ ወታደርን ክፉኛ አቆሰለ

የሁቲ አማጽያን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በኤደን ባህረ ሰላጤ ስትንቀሳቀስ የነበረች የጭነት መርከብ በየመን የሁቲዎች አማጺያን በተተኮሱባት ሁለት የክሩዝ ሚሳኤሎች ተመትታ አንድ መርከበኛ ክፉኛ ቆስሏል ሲል የአሜሪካ ጦር አስታወቀ።

የተጎዳው መርከበኛ ለህክምና ወደ ሌላ መርከብ በሄሌኮፕተር ተወስዷል ሲል የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንት ኮም) ዘግቧል።

ኤምቪ ቨርቤና የተሰኘችው መርከብ ሠራተኞች በመርከቧ ላይ የተነሳውን እሳት ለመቆጣጠር እየተረባተረቡ ነበር ብሏል። የዩክሬን ንብረት የሆነችው መርከብ በፖላንድ እንደምትተዳደር ተገልጿል።

ሴንትኮም አክሎም ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በቀይ ባህር ላይ ሁለት የሁቲ ጀልባዎች፣ አንድ መርከብ እና አንድ ሰው አልባ አውሮፕላን ማውደሙን ተናግሯል።

"እነዚህ በአካባቢው ላሉ የአሜሪካ፣ ለጥምር ኃይሎች እና ለንግድ መርከቦች ስጋት እንደሚደቅኑ ታምኗል" ሲል ሴንትኮም በመግለጫው ተናግሯል።

ሁቲዎች ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ኤምቪ ቬርቤናን ጨምሮ በሦስት መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተናግረዋል። ጥቃቱን የሰነዘሩት “በጋዛ ሰርጥ በወገኖቻችን ላይ ለተፈጸመው ወንጀል እና አሜሪካ እና ብሪታንያ በእኛ ላይ ላደረሱት ጥቃት የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት ነው” ብለዋል።

በኢራን የሚደገፈው ቡድን ከአንድ ቀን በፊት ቀይ ባህር ላይ የግሪክ ንብረት የሆነች መርከብን ኢላማ አድርጎ በውሃ መጥለቅለቋ ተገልጾ ነበር።

ታጣቂው የሁቲ ቡድን እራሱን በኢራን የሚመራ የእስራኤል፣ የአሜሪካ እና የሰፊው ምዕራባውያን የተቃዋሚ አካል አድርጎ ነው የሚመለከተው።

ከህዳር ወር ጀምሮ አማጺ ቡድኑ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸው መርከቦች ላይ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ ጥቃት እየፈፀመ ሲሆን ድርጊቱ በጋዛ የሚገኙትን ፍልስጤማውያንን ለመደገፍ ነው ብሏል።

አሜሪካ እና እንግሊዝ በበኩላቸው በየመን ውስጥ ባሉ የሁቲ ኢላማዎች ላይ ተከታታይ ጥቃቶችን አድርሰዋል። ይህም ታጣቂ ቡድኑ ከሁለቱ አገራት ጋር ግንኙነት አላቸው ብለው ባመኑባቸው መርከቦች ላይ አጸፋ እርምጃ እንዲወስዱ አድርጓል።

"ሁቲዎች በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያንን ወክለው እንደሚንቀሳቀሱ ቢናገሩም በጋዛ ካለው ግጭት ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው የሦስተኛ አገር ዜጎችን ኢላማ በማድረግ ህይወታቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ነው" ሲል ሴንትኮም ተናግሯል።

አማፂዎቹ በቀይ ባህር በኩል በሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ላይ ያደረሱት ጥቃት ተከትሎ ብዙ መርከቦች የጉዞ አቅጣጫ እንዲቀይሩ አድርጓቸዋል።

ረቡዕ ዕለት ሁቲዎች በቀይ ባህር ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ቱቶር የተባለች የላይቤሪያን መርከብ ቢያጠቁም፣ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አልደረሰም ተብሏል።