የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ "የግል አስተያየታቸውን ነው የሰጡት" - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው

የፎቶው ባለመብት, MoFA

የምስሉ መግለጫ, የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት ያለበትን ሁኔታ ያመለክታል የተባለው የኢትዮጵያ የቀድሞ ርዕሰ ብሔር ሙላቱ ተሾመ በአልጀዚራ ድረ ገጽ ላይ የጻፉት የግል አስተያየታቸውን መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ዛሬ አርብ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ "የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት በቀጠናው ላይ ያላቸውን ልምድ ተመርኩዘው የግል አስተያየታቸውን ነው የሰጡት" በማለት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እንደማይያያዝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የቀድሞ ርዕሰ ብሔር ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ከአንድ ሳምንት በፊት በአልጀዚራ ድረ ገጽ ላይ ባወጡት ጽሑፍ "የኤርትራ ፕሬዚደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ግጭት ለማባባስ እየሠሩ ነው" ሲሉ ከስሰው ነበር።

ይህንን ተከትሎም የኤርትራ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በማኅበራዊ መገናኛ ገጻቸው ላይ በሰጡት ባለ አስር ነጥብ መልስ ክሱን "ሐሰት" ሲሉ ማጣጣላቸው ይታወሳል።

የማስታወቅያ ሚኒስትሩ አክለውም የቀድሞውን ርዕሰ ብሔር ጽሑፍ "በክፋት የታቀደ እና ጠብ አጫሪ" ሲሉ ኮንነውታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሳይሰጥ ቆይቶ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በነበረ መደበኛ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት የግል አስተያየት መሆኑን በመግለጽ ጉዳዩን ከኢትዮጵያ መንግሥት አርቀውታል።

ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) አልጀዚራ ላይ በአፍሪካ ቀንድ ሌላ ግጭትን ለማስወገድ ጊዜው አሁን ነው በሚል ርዕስ ባወጡት ጽሑፍ የኤርትራ መንግሥትን በብርቱ ተችተዋል።

"ጦርነት የኤርትራ መንግሥት ዐቢይ ሥራው እና የተጠመደበት ጉዳይ ነው" ሲሉ ነበር በጽሑፋቸው ላይ ያሰፈሩት።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባዩ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች በሰጡት መልስ ላይ ይህ የቀድሞ ፕሬዝዳነት ጽሑፍ እና የኤርትራ ምላሽ የተነሳ ሲሆን፣ ከሳምንት በኋላ በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም አሳውቀዋል።

"ኢትዮጵያ እንደ መታደል ከአንድ በላይ የቀድሞ የምትላቸው ፕሬዝዳንቶች ያሏት አገር ናት" ያሉት ቃል አቀባዩ ጽሑፉ የቀድሞው ፕሬዝዳንት የግል አስተያየት መሆኑን አመለክተዋል።

ከኢትዮጵያን መንግሥት ጋር በተያያዘ በተለያዩ መድረኮች ላይ የሚገኙት የቀድሞው ፕሩዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶር) የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ እንዲሁም በአካባቢው ሰላም ላይ አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን በመጥቀስ ከስሰዋል።

የቀድሞው ርዕሰ ብሔር ደም አፋሳሹን የትግራይ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶሪያውን ግጭት የማቆም ስምምነት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ ብሎም በአካባቢው ላይ ማሳደር ለሚፈልጉት ተጽዕኖ እንቅፋት አድርገው እንደሚመለከቱት እና ጦርነቱ እንዲቀጥል ፍላጎት ነበራቸውም ብለዋል።

እንዲሁም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአሁኑ ወቅት በህወሓት መሪዎች መካከል የተፈጠረውን ክፍፍል ሊጠቀሙበት እንደሚፈልጉ እና በአማራ ክልል ውስጥ ሚሊሺያ እንዲፈጠር አድርገዋል በማለትም ወንጅለዋቸዋል።

ሙላቱ ተሾመ፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ውስጥ እጃቸውን እያስገቡ መሆናቸውን በጽሑፋቸው በመጥቀስ ወቅሰዋል።

ይህንን ክስ በተመለከተ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል፤ የኢትዮጵያ መንግሥት "ባለፉት ወራት" በአሥመራ ላይ "ምክንያት የለሽ እና የተጠናከረ የትንኮሳ ዘመቻ ከፍቷል" በማለት ከስሰዋል።

ኢትዮጵያን ቀጣናውን "የከበቡት" ችግሮች "መፍለቂያ እና ማዕከል ናት" ሲሉ የከሰሱት ሚኒስትሩ የማነ፤ አገራቸው በኢትዮጵያ "የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት" እንደሌላት ገልጸዋል።

ዶ/ር ሙላቱን "ታሪካዊ ሁነቶችን አዛብቶ በማቅረብ" የከሰሱት የኤርትራው ሚኒስትር፤ አገራቸው በትግራዩ ጦርነት የተሳተፈችው "ህወሓት በኤርትራም ላይ መጠነ ሰፊ እና በየደረጃው የሚከናወን ጥቃት የመፈጸም ዕቅድ" ስለነበረው እንዲሁም "በኢትዮጵያ መንግሥት ግብዣ" መሆኑን ገልጸዋል።

የማስታወቂያ ሚኒስትሩ፤"ቀጣናውን የከበቡት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ችግሮች የሚፈልቁት እና ማዕከላቸውን የሚያገኙት በኢትዮጵያ እንጂ በሌላ ቦታ አይደለም" ብለዋል።

በአገሪቱ ያለውን "ግጭት ምንጩ ከውጭ በማስመሰል ወይም ኤርትራን ማምለጫ በማድረግ" በአገሪቱ ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሔ እንደማይገኝም ሚኒስትሩ አቶ የማነ በጽሑፋቸው ላይ አስፍረዋል።

ለሁለት ዓመት በተካሄደው የትግራይ ጦርነት በትብብር የተሳተፉት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት ግንኙነት ጦርነቱን ካስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ግንኙነታቸው ተቀዛቅዞ ቆይቷል።