የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ

ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ በ7 ነጥብ ከፍ ብሎ በ43 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ የሚገኘው የሰሜን ለንደኑ አርሰናል ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ኒውካስትልን ያስተናግዳል።
አርሰናል የነጥብ ልዩነቱን ለማስጠበቅ ኒውካስትል ደግሞ ደረጃውን በተከታዩ ማንችስተር ዩናይትድ ላለመነጠቅ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአርሰናሉ የፊት መስመር ብራዚላዊው ጋብሬል ጂሰስ በዓለም ዋንጫ ባጋጠመው ጉዳት እስከ የካቲት መጨረሻ ወደ ጨዋታ አይመለስም።
ጂሰስን ተክቶ የሚጫወተው ኤዲ ኒኪታህ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ተሰልፎ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ይህ ለአርሰናል ተስፋ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
በሌላ በኩል ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ሽንፈትን ያላስተናገደው ኒውካስትል ደረጃውን ለማስጠበቅ እና በአሸናፊነቱ ለመቀጠል አርሰናልን ይፈትናል ተብሏል።
ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ኒውካስትል አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አርሰናል በአራቱ የበላይነት ነበረው። የዛሬው ጨዋታ ምሽት 4፡45 በአርሰናል ሜዳ ኤሚሬትስ ላይ ይደረጋል።
በተመሳሳይ ምሽት 4፡45 ኤቨርተን ከብራይተን ይጫወታሉ።
ባለፈው ቅዳሜ የፍራንክ ላምፓርዱ ኤቨርተን ሳይጠበቅ ማንችስተር ሲቲን ነጥብ በማስጣል ለመሪነት በሚያደርገው ጉዞ ላይ ተጨማሪ የቤት ሥራ ሰጥቶታል።
ብራይተን ደግሞ አርሰናልን አስተናግዶ 4 ለ 2 ቢሸነፍም በኳስ ቁጥጥሩ በተለይ ከሁለተኛው አጋማሽ በኋላ የተሻሉ ሆነው አምሽተው ነበር።
ሁለቱ ቡድኖች ባለፉት አምስት ጨዋታዎቻቸው ሦስቱን በማሸነፍ ኤቨርተን የበላይነት አለው።
ብራይተን አንድ ጊዜ አሸንፎ በአንዱ ነጥብ ተጋርቷል። ዛሬ በሚያደርጉት ጨዋታ ባለሜዳው ኤቨርተን ወደ ወራጅ ቀጠና ላለመንሸራተት ብራይተን ደግሞ ደረጃውን ለማሻሻል ይፋለማሉ።
በሌላ ጨዋታ አስደናቂ ጉዞ እያደረገ ያለው ፉልሃም ወደ ኪንግ ፓወር ስታዲየም አምርቶ ሌስተር ጋር ይፋለማል።
በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ዋዜማ ካደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሌስተር ሁለቱንም ሲሸነፍ ፍልሃም ደግሞ በሁለቱም ድል አድርጓል።
በዚህም ፍልሃም ደረጃውን ወደ 8ኛ ከፍ ሲያደርግ ሌስተር ደግሞ ወደ 13ኛ ወርዷል። ሁለቱ ቡድኖች ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሲገናኙ ሌስተር ሦስቱን በማሸነፍ የተሻለ ታሪክ አለው።
ፍልሃም ደግሞ አንዱን አሸንፎ በሌላኛው ነጥብ ተጋርቷል። ጨዋታው ምሽት 4፡45 ይጀመራል።
የምሽቱ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ማሳረጊያ በማንችስተር ዩናይትድ እና በርንማውዝ መካከል ይካሄዳል።
በተከታታይ ሽንፈት ውድድሩን የጀመረው ማንችስተር ዩናይትድ ከፍተኛ መሻሻል አድርጎ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ካለፉት አምስት ጨዋታዎችም ሽንፈትን ያስተናገደው በአንደኛው ብቻ ነው። ተጋጣሚው በርንማውዝ ደግሞ ከአምስት ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ ብቻ አሸንፎ በአራቱ ተሸንፏል።
ምሽት አምስት ሰዓት ኦልድ ትራፎርድ ላይ የሚደረገው ይህ ጨዋታ ለማንችስተር ዩናይትድ ከአንድ እስከ አራት ባለው እርከን ውስጥ ለመቆየት ወሳኝ ነው።
በርንማውዝ ደግሞ ከወራጅ ቀጠና ስጋት ለመውጣት ድሉ ያስፈልገዋል።












