በጎሳ ግጭት ምክንያት ባዶ የሆነው መንደር

ታትሟል

ከርቀት ሲታይ ሕይወት የሚገማሸርበት ቆንጆ የመኖሪያ መንደር ነው።

በአንድ አካባቢ እጅብ ብለው የተሰሩ መኖሪያ ቤቶች ይታያሉ።

ቀረብ ብለው ሲያዩት ግን መንደሩን የሞሉት የተቆለፉ የግቢ በሮች፣ ያልታረሱ ማሳዎች፣ እንዲሁም ያልተሰበሰበ የጫት ምርትን ጨምሮ ሰዎች ለአጥር የተከሏቸው ዛፎች ብቻ ናቸው።

የሰው ድምጽ አይሰማም። ከብቶችም የሉም። በመንደሩ ውስጥ የሚያፏጨው ንፋስ ብቻ ነው።

ከርቀት ለሚያየው መንደሩ ሕይወት እስከነ ሙሉ ወዟ የምትፍለቀለቅበት መኖሪያ ይመስላል። ጠጋ ብሎ ለሚያየው ግን ኦና ነው።

ነዋሪዎቹ ግጭት ሸሽተው ጥለውት የሄዱት መንደር።

እዚህ ቀዬ ምን አንደተከሰተ ለመጠየቅ የሚሻ ቢኖር የዐይን እማኝ ማግኘት ይከብዳል።

ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የአካባቢው አስተዳደርም ግጭቱ እየተባባሰ ሲሄድ ሸሽቶ ሄዷል።

ይህ አካባቢ ሀሮቦታ ይባላል። በሰሜን ኬንያ በመርሳቤት ግዛት [ካውንቲ]፣ ከመርሳቤት ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል።

ይህ መንደር ኬንያን ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ሚያዋስነው ሞያሌ በሚወስደው መንገድ፣ ከመርሳቤት ከተማ ሁለት ኪሎ ሜትር ብቻ ሲቀረው የሚገኝ ነው።

በዚህ መንደር ደም አልፈሰሰም። ነገር ግን ንብረት ወድሟል። በግጭቱ ምክንያት የተገደለ የለም፤ የእናቶች እንባ ግን ፈሷል።

የቦረና እና የገብራ ጎሳዎች ግጭትን ተከትሎ የመንደሩ ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ ቀያቸውን ለቀው ሸሹ።

ለረዥም ወራት ማቄን ጨርቄን ሳይሉ መንደራቸው ትተው ከሸሹት መካከል ከአንድ እጅ ጣት የማይበልጡ ሰዎች ብቻ ተመልሰዋል።

በቅርብ ጊዜ ወደ መኖሪያ መንደራቸው ከተመለሱት መካከል ወ/ሮ ናዎ ኢሳቆ “እኔ እዚህ አካባቢ ነበር የምኖረው። ግጭቱ ነው ከመንደሬ የነቀለኝ” ይላሉ።

የ11 ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ናዎ ሌላ መንደር ሄደው ተጠልለው ነበር የቆዩት።

ነገር ግን የቤት ኪራይ ሲጨምር፣ ኑሮ እየከበዳቸው ሲመጣ፣ የግጭት ስጋት ቢያሳስባቸውም ጨክነው ወደ ጎጇቸው ተመለሱ።

ከ60 በላይ አባወራዎች በሚኖሩባት መንደር የአካባቢው ዋርካ ናቸው የሚባሉ ሁሉ አሁን የሉም።

“ስድስታችን ገብተን ሰባተኛው አባወራ ተመልሶ ሸሸ” የሚሉት የስድስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ አወሊዎ ደንቢ ናቸው።

ወ/ሮ አወሊዎ የወ/ሮ ናዎ ጎረቤት ናቸው።

እርሳቸውም ወደ መኖሪያ ጎጇቸው የተመለሱት ሁለት ልብ ሆነው ነው።

“በሠላም እየኖርን፣ ግጭት ሲቀሰቀስ ተሰደድን። ሀለኬ ዋቆ መንደር ቤት እያቃጠሉ፣ በዳባ መንደርም እንዲሁ ቤት ንብረት ሲያቃጥሉ ለሕይወታችን ሰግተን ሸሸን።”

አሁንም ከተመለሱ በኋላ ስጋት ልባቸውን ፈትሮ ይዞታል።

“ከመሬታችን መሄድ አንፈልግም፤ ደግሞ ስጋቱ አልለቀቀንም። ጎረቤቶቻችን ሁሉም ስላልተመለሱ ፍርሃት ይዞናል። በአሁኗ ደቂቃ ራሱ ስጋት ውስጥ ነው ያለሁት።”

የኬንያ ምርጫ ተስፋ ብቻ አልያዘም፤ ግጭትም አርግዟል። ስጋት በልባቸው በር ስንጥቅ ያፏጫል።

የግጭቱ ዕለት

አቶ ሄኖክ ከሎ የጂሪሚ አካባቢ አስተዳዳሪ ናቸው። የሃሮቦታ መንደር በእርሳቸው አስተዳደር ስር ነው።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2021 በሰባተኛው ወር በአካባቢው ግጭት መቀስቀሱን ያስታውሳሉ።

በቅርብ ባለው መንደር ተማሪዎች በግጭት ምክንያት መገደላቸውን አስተዳዳሪው ይናገራሉ።

“ሁለት ወጣቶች እና አንድ ትምህርት ቤት የምትሄድ ታዳጊ ተገደሉ። ከዚያ በኋላ ግጭቱ ተነሳ። በሁላዳባ መንደር ቤቶች ከተቃጠሉ በኋላ፣ ሜዳ ላይ፣ በየነዋሪዎቹ ቤት እንዲሁም መንገድ ላይ ሰዎች ተገደሉ። ችግሩ ሲከፋ እኔም እንደ አስተዳዳሪ ከመንደሩ ሸሽቼ፣ ቤቴን ጥዬ ከተማ ገባሁ” ይላሉ።

ነዋሪዎች በእነርሱ ቀዬ ግጭቱ ንብረት ቢያወድምም፣ ሰዎች ግን ባለመሞታቸው ደስ ይላቸዋል።

ነገር ግን መንደርተኛው ከሞት ጠንካራ መንጋጋ ቢተርፉም፣ ባለ ጠብመንጃዎች ግን ንብረታቸውን በጠራራ ፀሐይ ዘርፈዋቸዋል።

ወ/ሮ ናዎ “ሌላ ጊዜ መጥተው 21 ፍየሎች ወሰዱብኝ” ሲሉ ይናገራሉ።

ከመንደራቸው ሸሽተው ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ ለስድስት ወር ያህል ኖረዋል።

እርሳቸው ወስነው ወደ ቀያቸው ቢመለሱም፣ አስራ አንዱ ልጆቻቸው ግን አለመምጣታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአካባቢው አስተዳዳሪ አቶ ከሎ፣ “ሃሮቦታ አካባቢ ከስልሳ እስከ ሰባ የሚደርሱ አባወራዎች ይኖራሉ። የተመለሱት ግን ስድስት ብቻ ናቸው” ሲሉ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የኬንያ የፀጥታ አካላት መሰማራት

የኬንያ መንግሥት በመርሳቤት ግጭት ከፍቶ የሠላማዊ ሰዎች ግድያ ሲጨምር ችግሩን ለመቆጣጠር በሚል በግንቦት ወር ላይ የሰዓት እላፊ ገደብ አውጇል።

በዚህ የሰዓት እላፊ ገደብ የተነሳ አገሬው ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ አይችልም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፣ በሰዓት እላፊ ገደቡ ምክንያት በአካባቢው ሰላም እየተመለሰ ቢሆንም የንግድ እንቅስቃሴዎችን መጉዳቱን ይናገራሉ።

በአካባቢው ስለተጣለው የሰዓት እላፊ ወ/ሮ ናዎ ሲናገሩ “ጥሩ ነው፤ ትልቅ ለውጥ አለ፤ ሌላ ጊዜ እኮ መንገድ ላይ ሰው በነጻነት አይንቀሳቀስም፤ አሁን ግን እንደ ልብ ይንቀሳቀሳል” ይላሉ።

ወ/ሮ አወሊዎ በበኩላቸው “ሰዓት እላፊው ትልቅ ለውጥ አመጣ። የሰዓት እላፊ ባይኖር ወደታች ወርደን መንደር መኖር አንችልም ነበር። ከዚህ በፊት ተራራው ላይ ቆመን [ግጭት ሲቀሰቀስ የሚሸሹበት] መንደራችን ያለበትን ሁኔታ እናይ ነበር። አሁን እኮ መጥተን መንደራችን ውስጥ እየኖርን ነው።”

ነገር ግን ሁለቱም እናቶች በየቀኑ ፖሊስ አልያም ሌላ የፀጥታ አካላት በአካባቢያቸው ብቅ ብሎ ካላያቸው ስጋት መላ አካላቸውን ያርደዋል።

ወደ መንደሩ ከተመለሱ ስድስት አባወራዎች ውስጥ ሦስቱ የቦረና ጎሳ፣ ሦስቱ ደግሞ ከገብራ ናቸው።

የስድስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ አወልዬ ይህንን አስመልክተው ሲናገሩ “ከድሮ በተሻለ እንደውም አሁን ተቀራረብን፤ ‘እኛ ለእነርሱ፣ እነርሱ ደግሞ ለእኛ እንጂ ሌላ ማን አለን?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

በመርሳቤት የሰዓት እላፊ ከተጣለ እና የፀጥታ ኃይሎች በቋሚነት ከተመደቡ በኋላ በነዋሪዎች እጅ የሚገኝን የጦር መሳርያ ሰብስበዋል።

አቶ ሄኖክ ከሎ ከእርሳቸው አካባቢ ብቻ 15 የጦር መሳርያ ተሰብስቦ ገቢ መደረጉን ይናገራሉ።

በአካባቢው ከሚኖሩ የተለያዩ ጎሳዎች መካከል ቦረና እና ገርባ ጎሳዎች በተደጋጋሚ የሚጋጩት በግጦሽ ቦታ እና በመሬት ነው።

የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ለግጭቱ መነሻነት ሁሌም የአካባቢው ፖለቲከኞችን ይከሳሉ።

የአካባቢው ነዋሪዎች በስፍራው የሰዓት እላፊ በመጣሉ ለውጥ እንዳለ ቢናገሩም አሁን ያለባቸውን ተጨማሪ ስጋት ግን አልሸሸጉም።

የስጋታቸው ምክንያት ደግሞ በሚቀጥለው ሳምንት በኬንያ በሚካሄደው ምርጫ የተነሳ ዳግም በጎሳዎቹ መካከል ግጭት እንዳይቀሰቀስ የሚል ነው።