ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከደኅንነት ኃላፊው ጉብኝት በኋላ ጠ/ሚ ዐቢይ ከሱዳን ባለሥልጣናት ጋር ተወያዩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳን የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት አባላት ጋር መወያየታቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታወቀ።
ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ወደ ሱዳን አቅንተው ከአገሪቱ ምክትል ወታደራዊ መሪ ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የልዑካን ቡድኑን አባላት ሰኞ ኅዳር 12/2015 ዓ.ም. በጽህፈት ቤታቸው ባገኙበት ወቅት በሁለቱ አገራት የጋራ ጉዳዮች መነጋገራቸው ተገልጿል።
ከአንድ ዓመት በላይ በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ውስጥ ያለችው ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በታላቁ ሕዳሴ ግድብና በድንበር ይገባኛል ምክንያት እንዲሁም በትግራይ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ ግንኙነታቸው ሻክሮ ቆይቷል።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ ሱዳንን አንስተው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሱዳን ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ ባገረሸው ጦርነት ውስጥ ምንም አይነት ሚና እንዳልነበራት ተናግረው ነበር።
የሁለቱ አገራት መሪዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ተገናኝተው በግንኙነታቸው ዙሪያ መወያየታቸው የተዘገበ ሲሆን፣ የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሃን ባለፈው ጥቅምት ወር በጣና ፎረም ላይ ለመሳተፍ ባሕር ዳር በመገኘት ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል።
ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ካርቱም ውስጥ ከአገሪቱ ምክትል ወታደራዊ መሪ ሌፍተናንት ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሐሜቲ) ጋር መነጋገራቸውን የሱዳን መንግሥት ዜና ወኪል ዘግቧል።
በውይይታቸውም በአገራቱ መካከል በደኅንነት እና በሌሎች ዘርፎች ስለሚደረግ ትብብር መወያየታቸውንና ሱዳንም በመንግሥት እና በህወሓት መካከል ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት ጄኔራሉ አድናቆታቸውን መግለጻቸው ተዘግቧል።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሚዋሰኑበት የአል ፋሽካ ለም የእርሻ መሬት ላይ ለዓመታት የቆየ የይገባኛል ጥያቄ የነበረ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊት ትግራይ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት በተቀሰቀሰበት ጊዜ ሱዳን ሠራዊቷን አሰማርታ አካባቢውን መቆጣጠሯ ይታወሳል።
በጦርነቱ ወቅትም ከሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሰርገው የሚገቡ ታጣቂዎች እንዳሉ በባለሥልጣናት ወቀሳ ሲሰነዘር ነበር።
በትግራይ ጦርነት ተወጥራ የቆየችው ኢትዮጵያ የሱዳን ሠራዊት ከያዛቸው የድንበር አካባቢዎች ለቅቆ እንዲወጣ እና በንግግር ችግሩ እንዲፈታ በተደጋጋሚ ስትጠይቅ የቆየች ቢሆንም፣ ከሱዳን በኩል ግን ግዛቱ እራሷ መሆኑን በመግለጽ ይዞታዋን ስታጠናክር ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ጄኔራል አል ቡርሐን ባለፈው ዓመት ኬንያ ውስጥ በተደረገው በኢጋድ ስብሰባ፣ ከወር በፊት ባሕር ዳር ላይ በጣና ፎረም እና ባለፈው ሳምንት ደግሞ ግብፅ በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ መገናኘታቸው ተዘግቧል።