ሁለት የእግር ኳስ ጨዋታዎች በዘረኝነት ምክንያት ተቋረጡ

የአየርላንድ ብሔራዊ ቡድን

የፎቶው ባለመብት, Inpho

ታትሟል

ሁለት ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ጨዋታዎች በዘረኝነት ምክንያት ሰኞ ዕለት በአጭሩ ተቀጭተዋል።

የመጀመሪያው ክስተት የተፈጠረው ኒው ዚላንድ ከካታር በነበራት ጨዋታ ነው።

የኒው ዚላንዱ ማይክል ቦክሳል በአንድ የካታር ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የዘረኝነት ጥቃት ደርሶብኛል ማለቱን ተከትሎ ጨዋታው ተገትቷል።

የሪፐብሊክ ኦፍ አየርላንድ ከ21 ዓመት በታች ከኩዌት አቻው የነበረው ግጥሚያም በተመሳሳይ የዘረኝነት ጥቃት ተቋርጧል።

የአየርላንድ እግር ኳስ ማሕበር እንደገለጠው አንድ የኩዌት ተጫዋች ተቀያሪ ወንበር ላይ የነበረን የአየርላንድ ተጫዋች ዘረኝነት የተሞላው ስድብ ሰድቦታል።

ሁለቱም ጨዋታዎች ኦስትሪያ ነበር የተከናወኑት። ኒውዚላንድ ካታርን 1-0 እየመራች ነበር። የአየርላንድ ከ21 ዓመታ በታች ቡድን ደግሞ ኩዌትን 3 ለምንም ሲመራ ቆይቷል።

“ማይክል ቦክሳል በመጀመሪያው አጋማሽ በካታር ተጫዋች የዘረኝነት ጥቃት ደርሶበታል” ሲል የኒው ዚላንድ ብሔራዊ ቡድን በትዊተር ገፁ አስፍሯል።

“ምንም ዓይነት እርምጃ ስላልተወሰደ ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ወደሜዳ ላለመለስ ወስኗል።”

የአየርላንድ እግር ኳስ ማሕበር ከኩዌት ጋር በነበረው ፍልሚያ የተፈጠረውን ክስተት ለፊፋና ለአውሮፓ አግር ኳስ ማሕበር እንደሚያሳውቅ ገልጧል።

የአየርላንድ እግር ኳስ ማሕበር ዛሬ ከ21 ዓመት በታች ከኩዌት ጋር በነበረው ጨዋታ አቋርጦ ወጥቷል። ይህ የሆነው የኩዌት ተጫዋች የኛን ተቀያሪ ተጫዋች ዘረኛ ንግግር በመናገሩ ነው” ይላል የማሕበሩ መግለጫ።

“ማሕበሩ ምንም ዓይነት የዘረኝነት ጥቃት የትኛውም ተጫዋቻችን ላይ እንዲደርስ አይፈቅድም። መሰል ክስተቶችን ለፊፋና ለዩኤፍ ያሳውቃል።”

ባለፈው ሳምንት የፊፋው ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የሪያል ማድሪድ ቪኒሲየስ ጁኒዬር ልዩ የፀረ-ዘረኝነት ኮሚቴ እንደሚመራ አሳውቀዋል።

ኮሚቴው፤ ያልተገባ ባሕሪ የሚያሳዩ ሰዎች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንዲወሰድ የሚመክሩ ተጫዋቾችን ያዘለ ነው።

ብራዚላዊው ቪኒሲየስ ጁኒዬር በስፔን ከባድ የዘረኝነት ጥቃት ሲደርስበት በግልፅ ወጥቶ “የስፔን እግር ኳስ ዘረኛ ነው” ብሎ መናገሩ ይታወሳል።