ሱቶን ዩናይትድ እና አርሰናል በኤፍ ኤ ዋንጫ እና በፕሪሚየር ሊግ ድል ያደርጋሉ አለ

ታትሟል

የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የፕሪሚየር ሊግ እና የኤፍ ኤ ዋንጫ ጨዋታዎችን ያስተናግዳሉ።

እንደተለመደው የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ የጨዋታ ግምቶቹን እንደሚከተለው አቅርቧል።

ኖቲንግሃም ከ ኒውካስል

ይህ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ይላል ሱቶን፤ ይህ ጨዋታ በደረጃ ሰንጠረዡ በሁለቱም ጫፍ ተቀምጠው ለሚገኙት ክለቦች ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል።

ኒውካስል የቻምፒየንስ ሊግ ሕልሙን ማሳካት የሚችለው በእንደዚህ አይነት ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦችን መሰብሰብ ሲችል ነው።

ፎረስት ምንም እንኳ በሜዳው ጥሩ ያለመሸነፍ ክብረ ወሰን ቢኖረውም በዚህ ጨዋታ በኒውካስል በጠባብ ውጤት እንደሚሸነፍ ሱቶን ግምቱን ሰጥቷል።

ግምት፡ ኖቲንግሃም 0 - 1 ኒውካስል

አስቶን ቪላ ከ ቦርንመዝ

ቦርንመዝ ከፕሪሚየር ሊግ ላለመውረድ የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ነው። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ይህን ማድረግ ይቻላቸዋል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር ይላል ሱቶን።

ሊቨርፑልን ያሸነፉት በርንመዝ ቪላንም በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ላይ ረትተው ነበር። አሁን ግን ቪላን ያሸንፋሉ ብዬ አልጠብቅም።

ግምት፡ ቪላ 2 - 0 ቦርንመዝ

ብሬንትፈርድ ከ ሌስተር

ሁሌም፤ መቼም ቢሆን ይህን ጨዋታ ብሬንትፈርድ ያሸንፋል ይላል ሱቶን።

ሌስተር አሁን ላይ እየታገለ ያለው ላለመውረድ ነው። ምንም እንኳ ባለ ብዙ ተሰጥዖ ተጫዋቾች ቢኖራቸውም ቡድኑ ግን ጎል ማስቆጠር አይችልም።

በአንጻሩ ንቦቹ ብሬንትፈርዶች በአግባቡ የተደራጁ ከመሆናቸውም በላይ የቆሙ ኳሶች ውጤታማ በማድረግ ስኬታማ ናቸው።

ግምት፡ ብሬንትፈርድ 2 - 1 ሌስተር

ሳውዝሃምፕተን ከ ቶተነሃም

ኬን በዚህ ጨዋታ ደምቆ ሊወጣ እንደሚችል ሱቶን ግምቱን ይሰጣል። ለዚህም ምክንያቱ ኬን በሳውዝሃምፕተን ሜዳ ያለውን ሪኮርድ በማስታወስ ነው።

ሃሪ ኬን በሳውዝሃምፕተን ሜዳ ባለፉት 15 ጨዋታዎች 11 ጊዜ ጎል አግብቶ 8 ኳሶችን ደግሞ ለግብ አመቻችቶ አቀብሏል።

ላለመውረድ እየተጫወቱ ያሉት ሳውዝሃምፕተኖች መሻሻልን ቢያሳዩም ሽንፈት የሚቀርላቸው አይመስልም ይላል ሱቶን።

ግምት፡ ሳውዝሃምፐተን 0 - 2 ቶተነሃም

ዎልቭስ ከ ሊድስ

ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው በመሎኒዩ በተገናኙ ጊዜ ብዙ ጎሎች ተቆጥረው ነበር። አሁን ግን ብዙ ጎል የሚቆጠር አይመስለኝም።

ሊድሶች ብዙ ችሎታ ያላቸው ተጫዋቾች ቢኖሯቸውም የሚያገኙትን ዕድል እየተጠቀሙ አይደለም። በዚህም የሊድስ ነገር ያሳስበኛል ይላል ሱቶን።

ዎልቭስ በተመሳሳይ ብዙ ጎል የሚያስቆጥር ቡድን ባይሆንም፣ ከዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ያገኛል የሚል እምነት አለኝ።

ግምት፡ ዎልቭስ 1 - 0 ሊድስ

ቼልሲ ከ ኤቨርተን

ቼልሲ አሁን ላይ ቅርጽ የያዘ ቡድን እየመሰለ ነው። ቅዳሜ ከሰዓት ከዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ መሰብሰብ ግድ ይላዋል።

ኤቨርተን በበኩሉ በሜዳው ጠንካራ በተቃራኒ ሜዳ ደግሞ ደካማ የሆነ ቡድን ሆኗል።

ግምት፡ ቼልሲ 2 - 0 ኤቨርተን

ማንችስተር ሲቲ ከ በርንሌይ

የኤፍ ኤ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ውድድር ማንችስተር ሲቲን ከ በርንሌይ አገናኝቷል። የዚህ ጨዋታ ትልቁ ትኩረት የቀድሞ የሲቲ ተጫዋች ቪንሰንት ኮምፓኒ በአሰልጣኝነት ወደ ኢትሃድ መመለሱ ነው።

በርንሌይ በቻምፒየንሺፕ አስደናቂ አቋም እያሳየ ያለ ክለብ ቢሆንም፣ ፔፕ ጋሪዲዮላ በኤፍ ኤ ዋንጫ ቀልድ ሰለማያውቁ እንግዳው ቡድን መሸነፉ አይቀሬ ነው ይላል ሱቶን።

ግምት፡ ማንችስተር ሲቲ 3 - 1 በርንሌይ

አርሰናል ከ ክርስታል ፓላስ

ይህ ተጠባቂ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ነው።

ሁለቱ ክለቦች ያሉበትን ወቅታዊ አቋም ለተመለከተ አርሰናል በሜዳው ፓላስን በቀላሉ ያሸንፋል ሊል ይችላል። ነገር ግን ፓላስ ከአርሰናል ሲገጥም ውጤት መገመት ሁሌም ከባድ ነው ይላል ሱቶን።

አሰልጣኝ ቪዬራን ያሰናበተው ፓላስ ባላፉት 4 ጨዋታዎች በኢሚሬትስ አልተሸነፉም። ግን ደግሞ ዘንድሮ በሊጉ ድል ካደረጉ በጣም ቆይተዋል። ማሸነፍ ቀርቶ ዒላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ እንኳ በቅጡ አያደርጉም።

ሦስቱ ነጥብ ዋንጫ ለመውሰድ እየተፋለመ ላለው አርሰናል የበለጠ ውድ ሊሆን ይችላል።

ግምት፡ አርሰናል 2 - 0 ክርስታል ፓላስ

ማንችስተር ዩናይትድ ከ ፉልሃም

ዩናይትድ እና ፉልሃም በኤፍ ኤ ዋንጫ ተፋጠዋል።

ያለ ካሰሚሮ ወደ ሜዳ የሚመለሰው ዩናይትድ በሜዳውም ቢሆንም በፉልሃም እንደሚፈተን ሱቶን ግምቱን ይሰጣል።

ፉልሃምም ቢሆን በአርሰናል የበላይነት ተይዞበት ከተሸነፈ በኋላ የሚደርገው ጨዋታ እንደመሆኑ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጥራሉ።

ግምት፡ ማንችስተር ዩናይትድ 2 - 1 ፉልሃም