በታሪካዊው የደቡብ አፍሪካ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ያጣው ኤኤንሲ ስልጣን መጋራት ይኖርበታል ተባለ

ታትሟል

ደቡብ አፍሪካን ለሶስት አስርት ዓመታት የመራው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) በምርጫው በፓርላማው የነበረውን አብላጫ ድምጽ በማጣቱ ስልጣን መጋራት ሳይኖርበት እንደማይቀር ተገለጸ።

የምርጫው አብዛኛው ውጤት ይፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጨቋኙን የአፓርታይድ ስርዓት መገርሰስ ተከትሎ አገሪቷን የመራው ኤኤንሲ መንግሥት ለመመስረት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር እንዲጣመር ይገደዳል።

በአብዛኛው፣ ከ99 በመቶ ባሉ የምርጫ ቀጠናዎች የድምጽ ቆጠራው የተጠናቀቀ ሲሆን ኤኤንሲ ያገኘው ድምጽ 40.25 በመቶ ነው። ከኤኤንሲ በመከተልም ዲሞክራቲክ አሊያንስ 22 በመቶ ድምጽ ማግኘት ችሏል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ፓርቲ ኡምኮንቶ ዊሲዝዌ (ኤምኬ) 15 በመቶ እና ሥር ነቀል ለውጥ በአገሪቱ ሊመጣ ይገባል የሚለው የጁሊየስ ማሌማ ኢኤፍኤፍ 9 በመቶ በማግኘት ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ናቸው።

ግንቦት 21 የተካሄደው የአገሪቱ ምርጫ ቆጠራ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ተጠናቆ ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግ የሚጠበቅ ቢሆንም 98 በመቶ ውጤቱ ይፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፓርቲው ብቻውን መመሥረት የሚያስችለውን የፓርላማውን አብላጫ ድምጽ ለመጀመሪያ ጊዜ አጥቷል።

የዘረኛው አፓርታይድ ስርዓት ማክተም ተከትሎ በትግሉ ወደ ስልጣን በአውሮፓውያኑ 1994 ወደ ስልጣን የመጣው ኤኤንሲ አገሪቷን በበላይነት ሲመራ ቆይቷል።

አገሪቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረገችው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ኔልሰን ማንዴላ ወደ ስልጣን የመጡ ሲሆን ከዚያ በኋላም በነበሩት ምርጫዎች ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ እያገኘ የአገሪቷ ዋነኛ ገዢ ፓርቲ ሆኖ ቀጥሏል።

ነገር ግን በአገሪቷ ውስጥ በተንሰራፋው ከፍተኛ ሙስና፣ የከፋ ስራ አጥነት እና ወንጀል መበራከት ምክንያት የፓርቲው ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሏል።

ለሶስት አስርት ዓመታት ያህል በነበሩት ምርጫዎች ለኤኤንሲ ድምጿን የሰጠች አንዲት ግለሰብ በዚህኛው ምርጫ ድምጿን ለዲሞክራቲክ አሊያንስ ሰጥታለች።

ግለሰቧ በአገሪቷ ባለው የከፋ የኑሮ ውድነት እና በተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ ምክንያት ኤኤንሲ ሙሉ በሙሉ ከስልጣን እንዲወገድ እንደምትፈልግ ለቢቢሲ ተናግራለች።

ምንም እንኳን ቀሪ ድምጽ ያልተቆጠረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ቢኖሩም ኤኤንሲ ብቻውን መንግሥት ለመመስረት የሚያስፈልገውን 50 በመቶ ድምጽ ሊያገኝ የሚችልበት መንገድ እንደሌለ የፖለቲካ ተንታኙዋ ሳኑሻ ናይዶ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ቆጠራው ሲጠናቀቅ ፓርቲው ሊያገኝ የሚችለው ድምጽ 45 በመቶ እንደሆነ ይጠብቃሉ። ፓርቲው በስልጣን ለመቆየት ከአንድ ወይም ከበርካታ ፓርቲዎች ጋር ጥምረት መፍጠር ይኖርበታል።

የኤኤንሲ ሊቀ መንበር ግዌዴ ማንታሼ ፓርቲያቸው በሁለተኛነት እየተከተለ ካለው የቀኝ ፖለቲካ ከሚያራምደው ዲኤ ጋር ጥምረት የመፍጠር ዕድሉ አነስተኛ ነው ብለዋል።

የጥምረት ስምምነት ለመፈጸም በሚፈልጉ ፓርቲዎች መካከል የፖሊሲ መጣጣም ሊኖር እንደሚገባው ገልጸዋል።

ለኤኤንሲ በዘረኛው አፓርታይድ ዘመን ሰውነትን የተነፈጉ እንዲሁም በምጣኔ ኃብት የተገለሉ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን የማብቃት ስራው “መደራደር የማይችልበት” ፖሊሲው ነው።

አክለውም ማንኛውም ጥምረት ለመመስረት የሚያልም አካል በቅርቡ በህግነት የጸደቀውን የብሔራዊ የጤና መድህን ሊስማማ ይገባል ብለዋል።

ዲኤ የጤና መድህንንም ሆነ የኤኤንሲን ጥቁሮችን የማብቃት ፖሊሲውን ይቃወማል።