በአድዋ ከተማ ለወራት ታግታ 3 ሚሊዮን ብር የተጠየቀባት ታዳጊ መገደሏን ፖሊስ አስታወቀ

ማኅሌት

የፎቶው ባለመብት, Million

ታትሟል

በትግራይ ክልል አድዋ ከተማ ባልታወቁ ግለሰቦች ታግታ ሦስት ሚሊዮን ብር ተጠይቆባት የነበራችው የ16 ዓመቷ ታዳጊ መገደሏን ፖሊስ ተገለጸ።

የአድዋ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተስፋዬ አማረ ረቡዕ ሰኔ 12/2016 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ማኅሌት ተኽላይ ተቀብራበታለች በተባለበት ቦታ በተካሄደ ቁፋሮ አስክሬኗን ማውጣቱን ገልጸዋል።

ፖሊስ ታዳጊዋ ተቀብራበታለች የተባለው ቦታ ጥቆማ የደረሰው ማኅሌት ተኽላይን በማገት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ታዳጊዋን ገድለው መቅበራቸውን አምነው የቀብር ቦታውን መርተው ካሳዩ በኋላ መሆኑን የፖሊስ ኃላፊው ተናግረዋል።

የ16 ዓመት ታዳጊዋ ማኅሌት ተኽላይ በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን አድዋ ከተማ መጋቢት 10/2016 ዓ.ም. ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ከታገተች በኋላ ሦስት ሚሊዮን የማስለቀቂያ ብር ተጠይቆባት ነበር።

ኃላፊው ፖሊስ የታዳጊዋ አስክሬን ተቀብሮበታል በተባለው ቦታ ላይ ቁፋሮ በማድረግ አስከሬን ያወጣ ሲሆን፣ ከስፍራው የታጋቿ ልብስ እና ጫማን ማግኘቱንም ገልጸዋል።

የአድዋ ከተማ ፖሊስ ኃላፊ ተስፋዬ አማረ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አስክሬኑ በቁፋሮ ከወጣ በኋላ የታዳጊዋ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ በባለሙያ ምርመራ እየተደረገበ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአድዋ ከተማዋ የሚገኙ የቢቢሲ ምንጮች እንደተናገሩት የማኅሌት ተኽላይ ቤተሰቦች መርዶው በፖሊስ ተነግሯቸው ሐዘን ተቀምጠዋል።

ማኅሌት ከሦስት ወራት በፊትን ነበር ወደ ትምህርት ቤት ብላ ከቤቷ ከወጣች በኋላ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታፍና መወሰዷን ታላቅ እህቷ ሚሊዮን ተኽላይ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ተናግራ ነበር።

ማኅሌት ታግታ በነበረችበት ወቅት ለቢቢሲ ቃለ መጠይቅ ያደረችው እህቷ ሚሊዮን፣ አጋቾቹ ታዳጊዋን ለመልቀቅ ሁለት ጊዜ ወደ አባቷ ስልክ ደውለው ነበር።

“ድምጿን አልሰማንም . . . አባታችንም ምን እንደሚፈልጉ እና እንዴት እንደሚሰጣቸው ጠይቋቸው ነበር። እነሱም ‘የምንልህን ለመስጠት ታዘጋጃለህ’ ካሉ በኋላ ስልካቸውን እየጠበቅን ነው” ብላ ነበር።

ማኅሌት በዚህ ዓመት ወደ ሁለተኛ ደረጃ የሚያሸጋግራትን የ8ኛ ክፍል ፈተና ለመውሰድ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተማረች ሳለ ነበር የታገተችው።

ቤተሰብ ወደ ቋንቋ ትምህርት ቤት በባጃጅ ስትጓዝ ታግታ የተወሰደችባቸውን ልጃቸውን “ሥነ ምግባር ያላት የቤት ልጅ” ሲሉ ይገልጿታል።

ከእገታው በኋላ አጋቾቹ በማኅሌት ስልክ ወደ ወላጅ አባቷ ስልክ በመደወል “ልጅህን በሕይወት ማየት የምትፈልግ ከሆነ ሦስት ሚሊዮን ብር አዘጋጅ” የሚል ትዕዛዝ ሰጥተው እንደነበረ ሚሊዮን ለቢቢሲ ገልጻ ነበር።

ማኅሌት

የፎቶው ባለመብት, MILLION

ማኅሌት ከታገተች በኋላ ቤተሰብ ልጃቸው ያለችበትን ቦታ እና አጋቾቿን ለማወቅ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች በታዳጊዎች ላይ የሚፈጸም እገታ እየተበራከተ ይገኛል።

ድርጊቱን የሚፈጽሙ ግለሰቦች አብዛኛውን ጊዜ እገታውን ለመፈጸም ባለ ሦስት ጎማ ተሽከርካሪዎችን እንደሚጠቀሙ ይገለጻል።

ቀደም ብሎ በመቀለ ከተማ በሚገኙ የተለዩ ክፍለ ከተሞች ከትምህርት ቤት ልጆች አግተው ሲወስዱ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች እንዳሉ የከተማዋ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።

ባለፈው ወር መጋቢት አቶ መሃሪ ከበደ የተባሉ ግለሰብ ልጅ የሆነ ህጻን ታግቶ ተወስዶ ቤተሰቦች አራት ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ተጠይቀው ነበር።

ህጻኑ ከአንድ ሳምንት በላይ በእገታ ስር የቆየ ሲሆን፣ ቤተሰቦች ከከተማዋ ፖሊስ ጋር በመተባበር ባደረጉት ጥረት ህጻኑ መጋቢት 17/2016 ዓ.ም. ተለቆ ከቤተሰቡ ጋር መቀላለቁን ቢቢሲ በወቅቱ ዘግቦ ነበር።