እውቁ ድምጻዊ ጀስቲን ቲምበርሌክ ጠጥቶ ሲያሽከረክር በፖሊስ ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Sag Harbor Police Department
እውቁ አሜሪካዊው ድምጻዊ ጀስቲን ቲምበርሌክ በኒው ዮርክ ውስጥ ጠጥቶ በማሽከርከር በፖሊስ ተይዞ እንደነበር የአካባቢው ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ገለጹ።
የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ማክሰኞ ማለዳ ተይዞ በይፋ ክስ እንደተመሠረተበት በኒው ዮርክ የሰፍሎክ አካባቢ አስተዳደር ዐቃቤ ሕግ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ቴምበርሌክ መጀመሪያ ላይ በቁጥጥር ሥር የዋለው በሎንግ አይላንድ ታዋቂ በሆነው የበጋ መዝናኛ ቦታ የሃብታሞች መንደር በሆነችው ሳግ ሃርበር ውስጥ ነው።
ድምጻዊው በይፋ ክስ ከተመሠረተበት በኋላ ያለዋስትና መለቀቁን የሶፍሎክ አካባቢ አስተዳደር ዐቃቤ ሕግ ጨምሮ ገልጿል።
የቲምበርሌክ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ከሆነ አቀንቃኙ ሰኞ ከዕኩለ ሌሊት በኋላ ቀይ መብራት የጣሰ ሲሆን በትክክለኛ የመንገድ መስመር ላይ ሳይጓዝ በመቅረቱ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የፖሊስ መኮንኖች ባስቆሙት ጊዜም ቲምበርሌክ ዐይን ኑ ከመቅላቱ በተጨማሪ ትንፋሹም ጠንካራ የአልኮል መጠጥ ጠረን እንደነበረው የፖሊስ ሰነድ ያስረዳል።
በተጨማሪም አነጋገሩ ዝግ ያለ እና ፖሊሶች የጠጣ ሰውን ለመለየት የሚጠቀሙበትን ዘዴ እንዲተገብር ሲደረግም በሚጠበቅበት ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ አልቻለም።
ድምጻዊው የአልኮል ትንፋሽ ምርመራ ለማድረግ ግን አሻፈረኝ ብሏል።
ቲምበርሌክ በፖሊሶች በተያዘበት ወቅት አንድ ብርጭቆ ማርቲኒ እንደጠጣ እና ጓደኞቹን ተከትሎ በመሄድ ላይ እያለ እንደነበር መናገሩ ተዘግቧል።
በሐምሌ ወር አጋማሽ በበይነ መረብ አማካኝነት ዳኞች ፊት እንዲቀርብም ቀጠሮ ተይዞለታል።
ጠበቃው ኤድዋርድ በርከር ጁኒየር ደንበኛውን በተገቢው ሁኔታ ለመከላከል እንደሚሠራ የተናገረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ከታሰረበት አካባቢ ዐቃቤ ሕግ ጋር በጋራ እየሠራ እንደሆነ ገልጿል።
የ43 ዓመቱ ቲምበርሌክ በቅርቡ ያወጣውን 6ኛ አልበም ተከትሎ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ጉዞ ለማድረግ ዝግጅት ላይ ነበር።
የአንድ ዝነኛ ባንድ አባል የነበረው ቲምበርሌክ ተዋናይ፣ የሙዚቃ ደራሲ እና ምርጥ ሽያጭ ካላቸው አርቲስቶች መካከል ነው።
ድምጻዊው ቀደም ሲል አብዝቶ በመጠጣት ይፈተን እንደነበር በግልጽ ተናግሯል።
በኒው ዮርክ ጠጥቶ ማሽከርከር አንድ ሺህ ዶላር እና ቢያንስ ለ6 ወር መንጃ ፍቃድ መነጠቅን ያስከትላል።
ቲምበርሌክ በቀጣዮቹ የእረፍት ቀናት በቺካጎ በመጪው ማክሰኞ ደግሞ በኒው ዮርክ የሙዚቃ ድግስ ለማቅረብ ቀጠሮ ይዞ ነበር።
አስር ጊዜ ግራሚን የተሸለመው ደምጻዊው በሁለት ፊልሞችም ላይ ተውኗል።
ቴምበርሌል ከታዋቂዋ ተዋናይት ጄሲካ ቢል ጋር በትዳር ውስጥ ያለ ሲሆን ሁለት ልጆችም አሏቸው።












