ተማሪዋን የገደለው ግብፃዊ በሞት ሲቀጣ በቀጥታ ቲቪ እንዲታይ ፍርድ ቤት ጠየቀ

አንዲት ተማሪን የገደለው ግለሰብ የሞት ቅጣት ሲፈጸምበት በቀጥታ በቴሌቭዥን እንዲታይ የግብፅ ፍርድ ቤት ጠየቀ።
የሞት ቅጣቱ ሲፈጸም በቀጥታ በቴሌቭዥን እንዲታይ የጠየቀው ፍርድ ቤት፣ ይህንን ሂደት ሕጋዊ ለማድረግ የሕግ አንቀጽ ማሻሻያ እንዲደረግም ጥያቄ አቅርቧል።
ሞሐመድ አደል የተባለው ግለሰብ ናይራ አሽራፍ የተባለችን ሴት በስለት ወግቶ ሲገድል የሚያሳይ ቪድዮ ባለፈው ወር ግብፅ ውስጥ ከተሰራጨ በኋላ ሕዝባዊ ቁጣ ቀስቅሷል።
ናይራ አሽራፍን ግለሰቡ የገደላት ከምትማርበት ዩኒቨርስቲ ውጪ ሲሆን፣ የፍቅር ጥያቄውን ባለመቀበሏ ነበር ሕይወቷን የቀጠፈው።
ድርጊቱን የሚያሳይ ቪድዮ ግብፅ ውስጥ በስፋት ከታየ በኋላ በርካቶች ቁጣቸውን ገልጸዋል።
የግብፁ ፍርድ ቤት ለአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባስገባው ደብዳቤ፤ የ22 ዓመቱ ሞሐመድ በሞት ሲቀጣ በቀጥታ ቴሌቭዥን እንዲተላለፍ ጠይቋል።
የሞት ቅጣቱ ሲፈጸም ቢያንስ የተወሰነው ክፍል እንኳን በቴሌቭዥን ቢተላለፍ መቀጣጫ እንደሚሆን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
ግለሰቡ ላይ የሞት ፍርድ የወሰነውም ይሄው ፍርድ ቤት ነው።
ግብፅ ውስጥ የሞት ቅጣት ተግባራዊ የሚሆነው እስር ቤት ውስጥ በሚፈጸም ስቅላት ሲሆን፣ ቅጣቱ በቀጥታ አይተላለፍም።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 የወጣ የተባበሩት መንግሥታት የዳሰሳ ጥናት እንደሚጠቁመው፣ ስምንት ሚሊዮን ግብፃውያን ሴቶች የጥቃት ሰለባ ናቸው።
የናይራ አሽራፍን ግድያ ተከትሎ በማንሱራ ግዛት የተካሄደውን የፍርድ ቤት ሂደት በርካታ ግብፃውያን ተከታትለውታል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መረጃ መሠረት፣ ግብፅ በ2021 በዓለም ላይ የሞት ቅጣት ከሚጥሉ አገራት በሦስተኛነት ተቀምጣለች።
ለግድያ ወንጀል የመጨረሻው ቅጣት ሞት ሲሆን፣ ቅጣቱ ሲፈጸም እምብዛም በአደባባይ አይታይም፤ በቴሌቭዥን የመተላለፍ ዕድሉም ውስን ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ በ1998 አንዲትን ሴት እና ሁለት ልጆቿን የገደሉ ሦስት ግለሰቦች የሞት ቅጣት ሲፈጸምባቸው በቴሌቭዥን መተላለፉ እንደተለየ አጋጣሚ ይጠቀሳል።
ግብፅ ወሲባዊ ጥቃት እንዲሁም ወሲባዊ ትንኮሳ በብዛት ከሚመዘገብባቸው አገራት አንዷ ናት።
ሴቶች ላይ ያነጣጠረ ግድያ (femicide) ጋር በተያያዘ የግብፃዊቷ የቴሌቭዥን መሰናዶ አቅራቢ ሻይማ ገማል ግድያ ተጠቃሽ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በግብፅ የጥቃት ሰለባ ናቸው ካላቸው ስምንት ሚሊዮን ሴቶች መካከል አብዛኞቹ ጥቃት የሚደርስባቸው በቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በፍቅር አጋሮቻቸው ነው።
በተጨማሪም በርካታ ሴቶች ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አደባባዮች በማያውቋቸው ወንዶች ትንኮሳ እንደሚፈጸምባቸው ሪፖርቶች አመልክተዋል።












