በግብፅ ሊደፍራት የሞከረን ሰው የገደለችው ሶማሊያዊት ታዳጊ ከእስር ተለቀቀች

ግብፅ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

ግብፅ ውስጥ ሊደፍራት ሞክሯል የተባለውን ‘የባጃጅ’ ሹፌር የገደለችው ሶማሊያዊት ታዳጊ ከእስር ተለቀቀች።

የ15 ዓመቷ ታዳጊ ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ ብላ ለፖሊስ እጇን መስጠቷን እና ለአራት ቀናት በእስር ላይ እንደነበረች የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የፖሊስ እና የሕክምና ምርመራ ታዳጊዋ ራሷን ለመከላከል የወሰደችው እርምጃ ሊሆን እንደሚችል ማሳየቱን የግብፅ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ገልጿል።

ሶማሊያዊቷ ታዳጊ ትላንት አርብ ከእስር መለቀቋ የተሰማ ሲሆን ተጨማሪ ምርመራ እንደሚደረግም ተሰምቷል።

ሟቹ የባጃጅ ሹፌር ታዳጊዋን ራቅ ወዳለ ስፍራ ወስዶ ለመድፈር መሞከሩን አህራም ሆንላይን የተባለ የግብፅ ሚዲያ ዘግቧል።

ሆኖም ከግለሰቡ ጋር ግብግብ የገጠመች ታዳጊዋ በቢላዋ ወግታው ከአከባቢው መሸሿ የተነገረ ሲሆን የእሷም እጅ መጎዳቱ ተዘግቧል።

ጉዳዩ በግብፅ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በኩል ከፍተኛ ትኩረት ያገኘ ሲሆን፣ ከፍተኛ ዝና ያላቸው ጠበቆች እና የመብት ተሟጋቾች ታዳጊዋን እንዲረዷት ጥሪ ሲያቀርብ ነበር።

በግብፅ ወሲባዊ ጥቃቶች በስፋት የሚከሰቱ ሲሆን፣ እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 የተባበሩት መንግሥታት ይፋ ያደረገው መረጃ፣ በአገሪቱ የሚገኙ 99.3 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ጾታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው አመልክቷል።

ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ጥቃት አድራሾች ላይ የሚጣሉ ቅጣቶች ላይ መሻሻሎች እንዳሉ ቢነገርም፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ሴቶችን የሚደፍሩ ሰዎች ላይ የተጠናከረ ምርመራ ባለማድረግ አሊያም ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ችላ በማለት ይወቀሳሉ።