ኢራን ሆርሙዝን ለመክፈት ከትራምፕ የጠየቀቻቸው ስድስት ቅድመ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢራንም ሆነ ኦማን በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን አስተዳደር በተመለከተ አዲስ ድርድር 'አዎንታዊ' ለውጥ ማሳየቱን እና ወደ መጨረሻው መቃረቡን ተናግረዋል።
ይህም የመርከብ እንቅስቃሴ ዳግም ሊጀመር ይችላል የሚል ተስፋን ፈንጥቋል።
ድርድሩ ኢራን እና ኦማን በጋራ የሚያስተዳድሩት በባህረ ሰላጤው ውስጥ አዲስ የመተላለፊያ መስመር መክፈት ላይ ያተኮረ ነበር።
ነገር ግን ስምምነቱ ሊፈረም ይችላል የሚል ተስፋ እየጨመረ በመጣ ቁጥር ኢራን ወሳኝ የሆነው የውሃ መስመር እንደገና ከመከፈቱ በፊት አሜሪካ ማሟላት አለባት ያለቻቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ዘርዝራለች።
አብዘኛዎቹ ቅደመ ሁኔታዎች በሁለቱ አገራት መካከል ሰኔ 10/2018 ዓ. ም. ከተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ አልፈው የሚሄዱ ናቸው።
ሌሎች ደግሞ ከዚህ በፊት የነበሩትን ቅድመ ሁኔታዎች የሚደግሙ ሆነው ከወሽመጡ መከፈት ጋር እንዲያያዙ ተደርገዋል።
ኢራን አሁን ያስቀመጠቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? አሜሪካ ማሟላት የምትችላቸው ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የኢራን የጠቅላይ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ፀሐፊ እና የአሁኑ የጠቅላይ መሪ አማካሪ መሐመድ ባገር ዞልጋድር ኢሪብ በተሰኘው ብሔራዊ የመገናኛ ብዙኃን ላይ በወጣው መግለጫ አሜሪካ ባህሪዋን "ማረም" እና ቅድመ ሁኔታዎቹን ማሟላት እንዳለባት አስጠንቅቀዋል።
መግለጫው 'የባህሪ ማስተካከያ' ማለት የሚከተሉት ነጥቦች ማለት መሆኑን ዘርሯል።
1. ኢራንን በምንም ዓይነት መንገድ ከማስፈራራት ወይም የዚህን አገር ክቡርነት ከመዝለፍ መቆጠብ
ኢራን፣ አሜሪካ ማስፈራራቷን እንድታቆም እና እንደዚህ ዓይነት ስጋቶች እንደገና እንደማይከሰቱ ዋስትና መስጠት እንዳለባት ጠይቃለች። ይህ በአብዛኛው የፖለቲካ እና የደህንነት ጥያቄ ነው። የተኩስ አቁም ስምምነት በሁለቱም ወገኖች በተዘዋዋሪ መንገድ ገደብ የሚጣልበት ቢሆንም፣ ወደፊት ለሚመጡ ስጋቶች በይፋ የሚጠይቁ ዋስትናዎች ቀደም ሲል በተዘገበው የጊዜያዊ ስምምነት ውሎች ውስጥ በግልጽ ከተገለጸው ይልቅ ሰፋ ብለው የቀረቡ ይመስላል።
2. በኢራን እና በሊባኖስ፣ ፍልስጤም፣ የመን እና ኢራቅ ውስጥ በሚገኙ አጋሮቿ ላይ የሚደረገውን ጦርነት እና ጥቃት እስከ ወዲያኛው እንዲቆም
ቴህራን በእርሷ ላይ ብቻ ሳይሆን በሊባኖስ፣ ፍልስጤም፣ የመን እና ኢራቅ ውስጥ ባሉ አጋሮቿ ላይም ወታደራዊ እርምጃ እንዲቆም አጥብቃ ጠይቃለች። በሰኔ ወር በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ላይ "ሊባኖስን ጨምሮ ሁሉም ግንባሮች" በሚል የተቀመጠው ሃሳብ ሌሎች አገሮችን የሚገልጽ ሲሆን ሰፋ ያለ ቀጣናዊ የደህንነት ዋስትናዎችን እንደሚያስፈልግም ያመለክታል።
3. የባህር ኃይል እገዳው ተነስቶ በኢራን ዙሪያ የሚገኙ ኃይሎች (የባህር እና የአየር ኃይል) ለቅቀው ይውጡ
በሰኔ ወር አሜሪካ እና ኢራን በተፈራረሙት ስምምነት መሠረት ዋሺንግተን በ30 ቀናት ውስጥ የጣለችውን እገዳ እንድታነሳ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ይህ ግን በቀጥታ ከባህር ወሽመጡ ዳግም መከፈት ጋር የተያያዘ አልነበረም።
4. በሁለቱም ጦርነቶች በኢራን ላይ ለደረሰው ጉዳት ሙሉ ካሳ መክፈል
ይህ የሚያመለክተው እአአ በ2025 የተካሄደው የ12 ቀናት ጦርነት እንዲሁም በየካቲት ወር ቴህራን ላይ የተከፈተውን ዘመቻ ነው። የካሳ ጉዳዮችን በሚመለከት ከሰኔው የመግባቢያ ስምምነት በኋላ በሚኖር ንግግር የሚታይ እንደሚሆን ይጠበቅ ነበር። ሆኖም ግን አሁን ቴህራን ካሳውን በቀጥታ ከሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ዳግም መከፈት ጋር በይፋ እያገናኘችው ነው።
5. በኢራን ሕዝብ ላይ የተጣሉትን 'ጭካኔ የተሞላባቸው እና ሕገወጥ' ማዕቀቦች አንሱ
የማዕቀብ እፎይታ የጊዜ ሰሌዳ ወደፊት በሚኖር ድርድር ውስጥ እንደሚካተት ይጠበቃል። ስለዚህ ኢራን እዚህ ላይ ሙሉ በሙሉ አዲስ ጉዳይ አላመጣችም። አዲስ የሆነው ነገር የማዕቀብ እፎይታ በግልጽ ከባህር መስመሩ መከፈት ጋር የተያያዘ ነው የሚለው ጽኑ አቋም ነው።
6. እንዳይንቀሳቀሱ የተደረጉትን እና የተዘረፉትን የኢራን ሕዝብ ንብረቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መልቀቅ
ይህ ፍላጎትም አዲስ አይደለም። የታገዱ ወይም እንዳይንቀሳቀሱ የተደረጉ በውጭ የሚገኙ የኢራን ሃብቶች መለቀቅ ቀደም ሲል ውይይት ተደርጎበታል።

የፎቶው ባለመብት, Elke Scholiers/Getty Images
ስድስቱ ቅድመ ሁኔታዎች ኢራን የባህር ወሽመጥ ዳግም ከመከፈቱ በፊት መሟላት እንዳለባቸው ጠቅሳለች።
የቢቢሲ የመካከለኛው ምስራቅ ተንታኝ ሴባስቲያን ኡሸር ይህ የኢራንን አቋም ማጠናከሩን ያሳያል ብለዋል።
"እነዚህ የመግባቢያ ስምምነቱ ማዕቀፍ አካል የነበሩ ሁኔታዎች ናቸው... ነገር ግን የጊዜ ሰሌዳው እና አፈጻጸሙ በጣም የተለያዩ ይመስላሉ።"
የሆርሙዝ ወሽመጥ "አሁንም እንደተዘጋ በመሆኑ" ቴህራን ጠንካራ አቅም እንዳላት ሊሰማት ይችላል ብለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ተቋም የሆነው የኩዊንሲ ኢንስቲትዩት ሥራ አስፈፃሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ትሪታ ፓርሲ ለቢቢሲ ወርልድ እነዚህ አቋሞች የተጋነኑ መሆናቸውን እና ምናልባትም የማፈግፈግ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ኢራናውያን ራሳቸውን እንደሚያውቁ ያምናሉ ብሏል።
"በይፋ የቀረበው ነገር በድርድር ጠረጴዛው ላይ ከሚንጸባረቀው ጋር ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል" በማለት ሃሳቡን ያጠናክራል።

የፎቶው ባለመብት, US Central Command / X
ፓርሲ "ይህንን ሂደት ለማራዘም እየሞከሩ ብቻ ሊሆን ይችላል" በማለት የድርድር ስልት ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል።
በአገዛዙ ውስጥ ያሉ ወግ አጥባቂ ግለሰቦች መካከል የተወሰኑት ኢራን በሰኔ ወር ስምምነት ላይ ለመድረስ በጣም ቸኩላለች የሚል እምነት እንዳለቸው ይናገራል።
ከዚያም ስምምነቱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ፈርሶ ጥቃቶች እና የአጸፋ እርምጃዎች ቀጥለዋል።
ፓርሲ እንደሚለው በኢራን ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ድርድሮች ለረጅም ጊዜ ተጓትተው ቢሆን ኖሮ የዓለም የነዳጅ ዋጋ የበለጠ ተባብሶ የዓለም አቀፍ የምጣኔ ሃብት ችግር ስለሚፈጠር ትራምፕ በኢራን ዒላማዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ላይሞክሩ ይችሉ ነበር የሚል ጠንካራ እምነት በወግ አጥባቂ ኢራናውያን ዘንድ አለ።
ስለዚህ ኢራን እንዲህ ዓይነት "ስህተት" ዳግም ለመስራት ፈቃደኛ አይደለችም ሲሉ ያስረዳል።
ይህ ሆኖ ግን በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ ስምምነት ሊደረስ ጥቂት ቀናት ብቻ እንደሚቀሩ አሁንም ግምቱን ያስቀምጣል።
መርከባቸውን ለማንቀሳቀስ የሚጠብቁ እንዲሁም የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ የሚማጸኑ ይህ ግምት ትክክል እንዲሆን ይመኛሉ።















