ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፖሊስ የቻይና ሰላይ ናቸው የተባሉትን የፊሊፒንስ ከንቲባ እያደነ ነው
በፊሊፒንስ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ግለሰብ የቻይና ሰላይ ናቸው የሚል ክስ ከቀረበባቸው በኋላ መደበቃቸውን ባለስልጣናቱ ተናገሩ።
ፖሊስ አሊስ ጉአንን የተሰኙትን ከንቲባ በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚታወቁ አድራሻዎቻቸው የእስር ማዘዣ ቢወስድም ሊያገኛቸው አልቻለም። ደብዛቸውም ጠፍቷል ተብሏል።
በከንቲባዋ የትውልድ ስፍራ ባምባን ለቻይና አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው የተባለ ህገወጥ የበይነ መረብ ጨዋታ (ቁማር) ድርጅት ጋር እጃቸው አለበት ተብሏል።
ይህ ድርጅት በህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሰዎችን በማሰር፣ አካላዊ ጥቃት እና እንግልት በማድረስ የተከሰሰ ሲሆን የበይነ መረብ 'ጌም'ን ይጠቀም የነበረው ለሽፋንነት ነው ተብሏል።
የከንቲባዋ ታሪክ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ እንደ ድራማ የታየ ሲሆን በቻይናዊ አባታቸው ዙሪያ እንዲሁም ቻይና ያስቀመጠቻቸው ሰላይ ናቸው የሚሉ ጥርጣሬዎችን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ምላሽ ሰጥተው ነበር።
በደቡባዊ ቻይና ባህር ይዞታ ጋር በተያያዘ እሰጣ ገባ ላይ ያሉት ቻይና እና ፊሊፒንስ የከንቲባዋ ጉዳይ ውጥረቱን ጨምሮታል።
የፊሊፒንስ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት አርብ ከንቲባዋ እና አንዳንድ የቤተቦቻቸው አባላት እንዲታሰሩ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
“ራሳችሁን ግለጹ መደበቅ እውነትን አያጠፋትም” ሲሉ ፓርላማው በከንቲባዋ ላይ የከፈተውን ምርመራ እየመሩ ያሉት ሴናተር ሪሳ ሆንቲቬሮስ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ምንም ስህተት አልፈጸምኩም የሚሉት ከንቲባዋ ቻይናዊ አባታቸው እና እና የፊሊፒንስ ዜግነት ያላቸው እናቷ ያሳደጓቸው በአሳማ እርሻ እንደሆነ ገልጸዋል።
ነገር ግን የምርመራው አካል የሆኑት የፓርላማ አባል ሸርዊን ጋቻሊያን ከንቲባዋ የቻይና ዜግነት ያላቸው እና ትክክለኛ ስማቸው ጉዎ ሁዋ ፒንግ የሚል እንደሆነ የስደት መዝገቦችን ዋቢ አድርገናል ብለዋል።
“እስርን ለማምለጥ ተደብቃለች። የእኛ ተከታታይ ቡድኖች ፍለጋቸውን ይቀጥላሉ” ሲሉ ሸርዊን ለሃገር ውስጥ ሬድዮ ተናግረዋል።
የእስር ማዘዣው በተፈረመበት ዕለት ከንቲባዋ ለመራጮቿ በፌስቡክ ላይ ባስተላለፉት መልዕከት በአካባቢው ለተወሰነ ጊዜ እንደማይኖሩ ጠቁመው ነበር።
“ከእያንዳንዳችሁ ጋር በአካል ባለመገናኘቴ ይቅርታ፤ ሁላችሁም ናፍቃችሁኛል” ያሉት ከንቲባዋ የማይኖሩት “በጊዜያዊነት” እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ከንቲባዋ በዚህ መልዕክታቸው ላይ “ራሳቸውን ቢያጡም” ወደ ፖለቲካ ህይወት መግባታቸው እንደማይጸጽታቸው ገልጸው ለአገራቸው ፊሊፒንስ ጥልቅ ፍቅር አለኝ ብለዋል።
የከንቲባዋ ጠበቃ ኒኮላ ጃሚላ ደንበኛቸው ከሚደረጉ ምርመራዎች ጋር እንደሚተባበሩ ለአካባቢው ቴሌቪዥን አስረድተዋል።